ጠንካራ ተቋማትን የመፍጠር ሕልም እና ጉዞ

17 Hrs Ago 205
ጠንካራ ተቋማትን የመፍጠር ሕልም እና ጉዞ

ኢትዮጵያ የታሪክ ሐብታም ከሆኑ ሀገራት መካከል ስሟ ቀድሞ ይጠቀሳል፡፡ ሀገሪቱ ካሏት ግዙፍ ታሪኮች መካከል ደግሞ የረጅም ዘመን የመንግስትነት ሥርዓት አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያላት የሥርዓተ መንግሥት ታሪክ ግን በዕድሜው ልክ ጠንካራ እና ወጥነት ያለው ሳይሆን በመንግስታት መለዋወጥ ውስጥ ውጣውረድ የበዛበት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት እየደመሰሱ የመቅዳት አባዜ ሲሆን ኢትዮጵያን ካስተዳደሩ መንግስታት መካከል ጥሎ ያልወደቀን ማግኝቱ ከባድ ነውና ከውጣውረዶቹ  አንዱ ሆኖ ይነሳል፡፡

እንዲህ ያለው ውጣውረድ ደግሞ  ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የተቋማት ግንባታ  እንዳይኖራት ያደረገ ክስተት ሆኗል፡፡

እነዚህ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው የመንግስታት ለውጥ የማያውካቸው ይልቁንም ለመንግስት አቅም የሚሆኑ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ይህን የማረጋገጥ ስራ በብዙ መልኩ ፈተና የበዛበት እንደሆነ ቆይቷል፡፡

የነበረውን የማፍረስ ችግር ጎልቶ የሚታየው አንዱ ሥርዓት ሄዶ ሌላው ሥርዓት ሲተካ መሆኑ ተቋማት በመንግስታት ለውጥ ውስጥ እየተጠናከሩ እንዳይሄዱ ትልቅ ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከተመሰረተችበት የረጅም ዘመን ጉዞ  አብላጫው  የጦርነት መሆኑ በተቋማት ግንባታ ውስጥ የሁልጊዜ እንቅፋት እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ጥንታዊ የመንግስት ሥርዓት ባለቤት ብትሆንም  የነበረውን የማፍረስ ችግር ፖለቲካዊ ኋላቀር ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

መንግሥታዊ ተቋማት መሠረታቸው ጠንካራ ካልሆኑ የግለሰቦች ተክለ ስብዕና ብቻ ገዝፎ ለዘላቂ የሀገረ  መንግስት ግንባታ የሚሰጠው ትኩረትም ሆነ ቁርጠኝነት እዚህ ግባ የማይባል ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያም ይህ ችግር በመኖሩ የሀገር ግንባታ ሒደቱ ላይ ስምምነቶች እንዳይኖር አድርጎት ቆይቷል።

የሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስ እና  መኖር የሚረጋገጠው  ሕግ አስከባሪ ተቋማት በጠንካራ መሰረት ላይ ሲገነቡ ነው፡፡ ዜጎች  መብታቸው የሆነውን አገልግሎትን በሥርዓት ማግኘት የሚችሉትም ተቋማቱ ሕግ አክብረው የሚሠሩበት ተቋማዊ ልዕልና ሲኖራቸው ነው፡፡

ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ ሊሠሩበት የሚችሉት ተቋማቱ ከሕግ ውጪ ዝንፍ እንዳይሉ ከአቅም ጋር እኩል የሚጓዝ ተጠያቂነት ሲሰፍን መሆኑ ግልጽ ነው።

የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲኖርው ለተቋማት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ በአንጻሩ  ደካማ የተቋማት ግንባታ በሥልጣን መባለግ፣ ዝርፊያ እና  ሥርዓት አልበኝነት ጉልበት እንዲያገኙ እድል ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲህ ያሉ ችግሮች አጋጥመው ዜጎችም ለፈተና ተጋልጠው ያወቃሉ፡፡

ለዚህ ምክንያት ሆኖ የሚጠቅሰው ኢትዮጵያ ከሥርዓት ወደ ሥርዓት ስትሸጋገር የገጠሟት ችግሮች ይፈቱ የነበረው በጠንካራ ተቋማት እና በሕግ ሳይሆን በግለሰቦችና ቡድኖች ፈቃደኝነት በተዳከሙ ተቋማት ውስጥ ተሆኖ ነው፡፡

እምነት የሚጣልባቸው እና ቅንነት ያለው ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ፖለቲካዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን የሚያስተካክሉት ድህነት የመቀነስ ሂደቱንም ቀላል ያደርጉታል፡፡

ጠንካራ ተቋማትን የገነቡ ሀገራት  መሪዎች ሀገርን በሥርዓት ሲመሩ፣ በሥልጣናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነትን  ሲያስቀድሙ ይስተዋላል፡፡ ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት ሲሸጋገሩም የሚመሩት በሕግ ብቻ ነው፡፡

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም  መረጃ  ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዝላንድ እና ዴንማርክን በጠንካራ ተቋሞቻቸው ተጠያቂነትን ያረጋገጡ እና የዳበረ የዴሞክራሲ ባለቤቶች ናቸው ይላቸዋል።

በእነዚህ ሀገራት ዜጎች በመንግስታቸው ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸውም መረጃው ይጠቅሳል። የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ደረጃ ከእነዚህ ሀገራት በጣም የራቀ ነው።

ለዚህ ምክንያት ሆኖ የተጠቀሰው ደግሞ አሜሪካውያን በመንግስታቸው ላይ ያላቸው እምነት ዝቅ እያለ በመምጣቱ ነው ይላል የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ።

በተቋማት ግንባታ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡት ታዳጊ ሀገራት ናቸው። ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር እና የፍትሕ እጦት ለሚባሉ የሥርዓት በሽታዎችም ተጋላጭ  ሆነው ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያም ታዳጊ ሀገራት የሚፈተኑበት ችግር  ችግሯ  ነው። ጠንካራና እምነት የሚጣልባቸው ተቋማት የመገንባት ስራዋም  የመንግስት ምስረታ ታሪኳን የሚመጥን ባለመሆኑ ገና ብዙ መስራት እንደሚገባት ግልጽ ነው።

ፖለቲካውን ከኋላቀርነት ነፃ ለማውጣት እንዲሁም ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረት  አቅምን የሚፈትን ነው። መንግስት ለዚህ ትልቁ ምክንያት ነፃና ገለልተኛ  እንዲሁም ጠንካራ  ተቋማት ባለመገንባታቸው እንደሆነ ተደጋግሞ ሲነገር  ይስተዋላል።

ተቋማት ነፃና ገለልተኛ  ሲሆኑ  ታማኝነት እና ሕጋዊነት መለያቸው ይሆናል። ዜጎችም በመንግስትና በሚያገለግሏቸው ተቋማት ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ይሆናል። ይህ ደግሞ ችግሮች ሁሉ በተቋማት ይፈቱልኛል ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል። የዚህ ውጤት ደግሞ ፖለቲካውን  ከኋላቀርነት ነፃ ያወጣዋል፤ ድህነትን የማሸነፍ ጥረትንም ቀላል ያደርገዋል።

ጦርነት እንደጥላ በሚከተላት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮችን  ጠንካራ ተቋማትን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ  የመፍታት ባሕል ተለምዷዊ  ይሆናል። ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር የሚታየው ደምስሶ የመቅዳት የቆየ ልማድም ቦታ ያጣል። ይህ ሁሉ እውን የሚሆነው  ግን ጠንካራ  ነፃና ገለልተኛ ተቋማት መገንባት ሲቻል ነው።

አሁን ላይ መንግስት ብቁ ሀገራዊ ተቋማት እንዳልተገነቡ በማንሳት ይህ ሂደት እንዲቆም ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ሂደትን መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ለዚህም በአንዳንድ ተቋማት ላይ የታየው አፍርሶ ከመገንባት ይልቅ ሪፎርምን ተከትሎ የመገንባት ስልት ብዙ ለውጦች እያሳየ ነው።

ይህ ደግሞ ሀገርን ከሚያጸናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እስከ ዴሞክራሲ ተቋማት ድረስ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን ለመፍጠር በመንግስት የተሰጠው ትኩረት እና ሥራውንም በትኩረት የመስራት ልምምድ ያሳየው ውጤት ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ሊያወጣት እንደሚችል ተስፋ አስይዟል።

 ይህ እቅድ ከግብ ከደረሰ  የሀገሪቱ ተቋማት ለዘመናት  ከተጫናቸው ድብርት  ነጻ ይወጣሉ፣ ይህም ሲባል ብቃት ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ታግዘው ለሕግ የበላይነት ተገዥ ይሆናሉ እንደማለት ነው።

ተቋማት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምኅዳሩን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ጠንካራ ተቋሞች ውጤታማ ውሳኔ ለመስጠት ማዕቀፍ የሚያዘጋጁ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ እና ግልጽነትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ ናቸው። ነገር ግን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ቀላል ስራ እንዳልሆነ እሙን ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሥርዓት መለዋወጥ መሠረታቸው የማይናጋ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት  ሁሉም የራሱን ጡብ ማስቀመጥ ይኖርበታል።

ለዚህም ነው ብልጽግና ሁለተኛ ጉባዔውን ሲያካሂድ ካስቀመጣቸው 8 ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች ውስጥ በሁለተኛ ተራ ቁጥር እንዲህ ያለው፦ “የተቋማት ግንባታ ስኬት ለውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብለን እኛ ብልፅግናዎች ከልብ እናምናለን። ከዚህ ጽኑ እምነት ተነሥተንም ዴሞክራሲን ተቋማዊና ሕዝባዊ ባሕል በማድረግ የሀገረ መንግሥት ቅቡልነትን ለማረጋገጥ ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብተናል።

በመሆኑም የተጀመረውን የተቋማት ሪፎርም በየዘርፉና በየደረጃው አጠናክረን በማስቀጠልና ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸውን ተቋማት በማባዛት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችንን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆምና ጠንካራ የዴሞክራሲ ባሕል ለመፍጠር አበክረን የምንሠራ ይሆናል።”

በዚህ ነጥብ መሰረት ሀገር እያስተዳደር የሚገኘው ብልጽግና የተቋማት ግንባታ ላይ በሰፊው መስራት አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ጽኑ እምነቱ መሆኑ የሚያመላክት ነው። በቀጣይም መንግስት ዋና ትኩረቱ ሆኖ ተቋማትን በሪፎርም እየገነባ ነጻ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ይሰራል ማለት ነው። ይህ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ የዘመናት ህመም እንዲፈውስ ሊያደርግ የሚችለው አንዱ መፍትሄ።

ንብርቴ ተሆነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top