"ፋጡማ ቆሪ" በወሎ አካባቢ ለነፍሰጡር ሴቶች የሚዘጋጅ ባህላዊ በገንፎ የታጀበ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው ስርዓቱ የወሎ ነፍሰጡር ሴቶች እርግዝናቸው 9 ወር ሲደርስ እናቶች የገንፎ እህል አዘጋጅተው በባህላቸው መሰረት ደግሰው አብረው እየበሉ የሚመራረቁበት ነው፡፡
የኢቢሲ ሪፖርተር መታሰቢያ ደረጀ ወደ ወሎ ደጋን አካባቢ ባቀናችበት ወቅት አንድ ለመውለድ የተቃረበች ነፍሰጡር ሴት ከመውለድዋ በፊት በባህሉ መሰረት ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ይደረግላታል የሚለውን ቅኝት አድርጋለች፡፡
ድሪያ የለበሱ እናቶች ቀድሞ ከተዘጋጀው ዱቄት ላይ እየወሰዱ ለብዙኃኑ እንዲበቃ አድርገው በትልቅ ድስት ገንፎ ሰርተው ያቀርባሉ፡፡ ሰብሰብ ብለውም ለነፍሰጡሩዋ ሴት በሰላም ተገላገይ፣ ልጅሽን ወልደሽ እቀፊ እያሉ ይመርቃሉ፡፡
ገንፎው ከልዩ ልዩ ሰብሎች የሚዘጋጅ ሲሆን ቅቤ፣ ተልባና ማር ታክሎበት በልዩ ሁኔታ ይዘጋጃል፡፡
በፕሮግራሙ እለት ከሀዋ ሰኢድ ቤት ዘንድ የሚገኙት ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ የተዘጋጀውን ማዕድ ይቋደሳሉ፡፡ ገንፎ ከመመገብ ሥርዓቱ በፊት ግን እጅ የማስታጠብ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ የታጠቡበትን ቆሻሻ ውኃም እየደፉ ክፉ ነገርን እንደቆሻሻው ወኃ እንዲያጸዳላቸው ይለማመናሉ፡፡
ምግቡ ተበልቶ ካለቀ በኋላም መመራረቁ ይቀጥላል፤ ፕሮግራሙም ይደምቃል፡፡ በድሪያ ደምቀው በአንድ የተሰበሰቡ ሴቶች በገበታ ተዘጋጅቶ የቀረበው ገንፎ ላይ እጃቸውን አስቀምጠው ዱዓ (ጾሎት) በማድረግ በፍቅር መቋደስ ባህላቸው ነው፡፡
ከተዘጋጀው ገንፎ ላይ እየተቀነሰ መጀመሪያ ነፍሰጡሯ እናት እንድትቋስ ይደረጋል፡፡
ፋጡማ ቆሪ የወሎ እናቶች የገንፎ ሥነ-ሥርዓት ፍቅር የተሞላበት ማህበረሰባዊ መስተጋብርን የሚፈጥር ድንቅ ስርዓት ነው፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ