የትግራይ ህዝብ ከትላንት ቁስሉ ሳያገግም ዛሬም በጦርነት ወሬ በፍርሃትና በሰቀቀን እንዲኖር በፍጹም ሊፈረድበት አይገባም ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን በመፍጠርና በመንከባከብ ውስጥ ያለው ሚና ጥልቅ ነው ብለዋል።
ትግራይ የስልጣኔ መነሻ እና የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ዋልታ ማገር መሆኑንም እንስተዋል::
የትግራይ ህዝብ በማይፋቅ ቀለም የተፃፈ ብሩህ ታሪክ ያለው ህዝብ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከምንም በላይ ደግሞ የአገሩ ወዳጅ፣ የሰላምና የብልጽግና ወዳጅና ሥራ ወዳጅ ህዝብ ነው ብለዋል።
ትግራይ የመንግስት አስተዳደር እና ሃገረ መንግስት ግንባታ የተጀመረበትና ተጠበቆ የቆየብትም ምድር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ::
የትግራይ ህዝብ ከምንም በላይ ሃገሩን ወዳድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሰላምም ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ህዝብ መሆኑንም የአደባባይ ሃቅ ነው ብለዋል::
እንዳለመታደል ሆኖ ባለፉት አንድ መቶ አመታት ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ባጋጠሙ ቅሬታዎች ምክንያት የትግራይ መሬት የጦርነት ምድር ሆኖ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተካሄዱ ጦርነቶችም የትግራይ ህዝብ ምን አገኘ ምን ተጠቀመ የሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል::
አሁን ላይ ትግራይ እና የትግራይ ህዝብ ከጦርነት ነፃ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ለሚነሱ ችግሮች ጦርነት ብቸኛ መፍትሄ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ይገባልም ነው ያሉት::
ትግራይ ብዙ ምሁራንን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ ፖለቲከኞችን እና ህዝባቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎችን አፍርታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይ የትግራይ ልሂቃን ልዩነታቸውን በመግባባትና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በፀጥታ፣ በአካዳሚ እና በሚዲያው የሚሳተፉ ሊሂቃን የትግራይ ህዝብ ከጦርነት የሚያገኘው ትርፍ እንደሌለ ተገንዝበው ሰላምን እንዲሰብኩ ጥሪ አቅርበዋል::
የሚስተዋሉ ችግሮችንም ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍታት እንደሚገባና ችግሮቹም የህዝብን አንድነት በሚያጠናክሩ መልኩ መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::
ከፌደራል መንግስትና ከሌሎች ኃይሎች ጋር የሚኖርን ልዩነት በህገ መንግስቱና በዴሞክራሲ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል::