የዓለም ጤና ድርጅት የአሜሪካን ከድርጀቱ አባልነት የመውጣት ውሳኔ ለማስቀልበስ የሀገራት መንግስታት ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት ከዲፕሎማቶች ጋር በተካሄደ ዝግ ስብሰባ ላይ አሜሪካ ከአለም የጤና ድርጅት ለመውጣት ያስተላለፈችውን ውሳኔ እንድትቀይር ለሀገራት መሪዎች ጥሪ ማቅረቡም ነው የተገለፀው።
በስብሰባው ላይ የቀረበው የበጀት ሰነድ የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ፕሮግራም በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ እደሆነ ያሳያል ተብሏል።
በስብሰባ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የፋይናንስ ዳይሬክተር ጆርጅ ኪሪያኩ ኤጀንሲው አሁን ባለበት መጠን ገንዘብ የሚያወጣ ከሆነ ድርጅቱ ከእጅ ወደ አፍ አይነት ሁኔታ ውስጥ ይሆናል ብለዋል።
አሁን ያለው የወጪ መጠን ከድርጅቱ የፋይናንስ አቅም አንፃር የማይቻል እየሆነ ስለመምጣቱም አክለዋል።
በተመሳሳይ የአሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት የመውጣት ውሳኔ ተከትሎ በዝግ ስብሰባው ላይ የተገኙት የጀርመን መልእክተኛ ቦሩን ኩመል “ጣሪያው እየተቃጠለ ነው፣ እና እሳቱን በተቻለ ፍጥነት ማቆም አለብን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በስብሰባው ላይ አሜሪካ ከአለም የጤና ድርጅት ከወጣች ስለ ዓለም አቀፍ የበሽታ ወረርሽኝ ወሳኝ መረጃዎችን እንደምታጣ ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ ከ 2024-2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ትልቁ ለጋሽ ሃገር ስትሆን 988 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጓ ተጠቅሷል።
ይህ የአሜሪካ የገንዘብ ድጎማ የዓለም ጤና ድርጅትን 14 በመቶ የበጀት ድርሻ እንደሚሸፍን የዘገበው አሶሼትድ ፕረስ ነው።
በሴራን ታደሰ