ብልፅግና ፓርቲ ሊያፈርስ የሚፈልገውን ብቻ ማፍረስ ሳይሆን አልቆ መገንባትንም አስቀድሞ የሚያስብ ፓርቲ ነው ሲሉ የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ብልፅግና ሊያፈርስ የሚፈልገው በርካታ ኋላቀር አሰራሮች እና ልምምዶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ቢያውቅም አልቆ መገንባትን አስቀድሞ የሚያስብ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
ፒያሳን ማፍረስ ሳይሆን አልቆ መገንባት የብልፅግና መለያው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ 60 ዓመታትን ያልተሻገረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ ዓመታት የነበረን የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንፈልገውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት የነበረበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ሀሁን ስንጀመር ብልፅግናን እስከፈጠርንበት ድረስ ያሉ ድካሞች ውድቀቶች ልንሻገራቸው ያልቻልናቸው አንድ ፓርቲ ለውጥ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ለውጥ መሪ መሆኑን አለመገንዘባችን ነው" ብለዋል፡፡
ለውጥ መፍጠር ብቻውን ለውጥ ለመመራት የሚያስችል ብቃት እስካልፈጠረ ድረስ የተሟላ የፓርቲ ህልውና አይኖረውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለውጥ መፍጠር ማለት ስላለው ችግር ድካም ውድቀት አብዝቶ መናገር ሳይሆን መፍትሄም ማፍለቅ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
"ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሃምሳ እና ስልሳ አመታት የነበረን የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፤ ልናፈርስ ልንንድ የፈለግነውን በብዙ ማስረጃ መክሰስ እንጂ ልንገነባ የምናስበውን ልናመጣ የምንመኘውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት ነበረብን" ብለዋል፡፡