የኦሮሚያ ክልል የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሥድስት ወራት የስራ ዕቅድ ክንውን ግምገማ በአዳማ ገልማ አባ ገዳ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ፣ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ፣ የክልሉ መንግሥት አመራር አባላት፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳዳሪዎች በግምገማ መድረኩ ተገኝተዋል።
ግምገማው የክልሉ መንግስት ያለፉት ሥድስት ወራት የመንግሥትና የፓርቲ አፈጻጸም ላይ አተኩሮ የሚካሄድ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም ለህዝብ ቃል የተገቡና መንግስት ለመተግበር ያቀዳቸውን ስራዎች እውን ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በስራዎቹ ሂደት የነበሩትን ጥንካሬዎች በማስቀጠል ክፍተት የታየባቸው ተግባራት ላይ አመራሩ ጠንክሮ መስራትና የአመራርነት ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በቀጣይ ቀናት በሚደረገው የአመራሮች ውይይትም የፖለቲካ ስብራት መጠገን፣ የኢኒሼቲቭ ልማቶች ውጤታማነት፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አመራሩ መወያየት እንዳለበት አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በመድረኩም በክልሉ የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ የስራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ክፍተት በታየባቸው ነጥቦች ላይ አመራሩ ውይይት ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።