ስኬት በጠንካራ ሥራ ብቻ እንደሚገኝ የሚያስተምረው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሕይወት

2 Hrs Ago 423
ስኬት በጠንካራ ሥራ ብቻ እንደሚገኝ የሚያስተምረው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሕይወት

ማዴራ ከምትባል አንዲት ትንሽ መንደር ተነስቶ ዓለምን ያስጨበጨበ ስኬት ላይ የደረሰው ክርስቲያኖ ሮናልዶ 40 ዓመቱን ደፍኗል። በጣም አስገራሚው ነገር ግን ዛሬም በ20ዎቹ ዕድሜ እንደሚገኙት ተጫዋቾች ነው ኳስን የሚጫወተው። በእግር ኳስ ሕይወቱ ያላገኘው ሽልማት የለም፤ ከዓለም ዋንጫ በስተቀር ያላሳካው ዋንጫም የለም።

ይህን ሁሉ ያሳካው ሮናልዶ ግን እዚህ የደረሰው አልጋ በአልጋ በሆነ ጉዞ አይደለም። የተወለደው እ.አ.አ ፌብሩዋሪ 5 ቀን 1985 በፖርቱጋሏ ማዴራ በምትገኝ ፉንቻል በምትባል መንደር ከድሃ ቤተሰብ ነው።

 

እናቱ ምግብ አብሳይ ሆነው ይሠሩ የነበረ ሲሆን፣ አባቱ ደግሞ በአካባቢው በሚገኝ ክበብ ውስጥ ይሠሩ ነበር። በኋላም ልጃቸው ትልቅ እንዲሆንላቸው ሲንከባከቡት የነበሩት አባቱ እሱ ገና ለጋ ሳለ ሞቱ። እናም ሁሉም ኃላፊነት በእናቱ ላይ ወደቀ። እሱም እናቱን ለመርዳት ጎዳና እስከማጽዳት የደረሰ ሥራ መሥራት ጀመረ። 

ጎን ለጎንም የቀጣይ ስኬቱ መዳረሻ የሆነውን እግር ኳስን መጫወቱን ቀጠለ። በ12 ዓመቱም የስፖርቲንግ ክለብ አካዳሚ ውስጥ የመግባት ዕደሉን አገኘ። ከተወለደበት አካባቢ ለቅቆ ክለቡ ወደሚገኝበት ሊዝበን ካመራ በኋላ የነበረው ቆይታው ከባድ ቢሆንም እሱ ግን እጅ ሳይሰጥ ነገው ላይ ብቻ አተኩሮ ጠንክሮ መሥራቱን ቀጠለ። 

በአንድ ዓመት ውስጥም ለስፖርቲንግ ከ16፣ ከ17፣ ከ18 ዕድሜ በላይ ቡድኖች ተጫውቶ በማሳመን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለ ብቸኛው ተጨዋች ሆነ። ይህ ፈጣን ለውጡም ቀጣይ የእግር ኳስ ሕይወቱ ማሳያ ነበረ። የሚያስጨንቃቸውን ተቀናቃኝ የሚወዱት የቀድሞው ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ክለባቸው ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተከላካዮቻቸውን ሲያስጨንቃቸው የነበረ አንድ ታዳጊ ትኩረታቸውን ሳበው።

 

ማንችስተር ዩናይትድም እ.ኤ.አ በ2003 በወቅቱ የተጨዋቾች የዝውውር ዋጋ ውድ በተባለ 12.24 ሚሊዮን ፓውንድ ታዳጊውን አስፈረመ። በፈረመ በዓመቱም ከክለቡ ጋር ኤፍኤ ካፕን አሸነፈ። ሮናልዶ ከ2006 እስከ 2009 በተከታታይ ከማንችስተር ዩናትድ ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል። 

በ2008 ደግሞ የመጀመሪያውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከክለቡ ጋር ያሸነፈ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት የባሎንዶር ተሸላሚም ሆኗል። በስድስት ዓመት ማንችስተር ዩናይትድ ቆይታውም 292 ጨዋታዎችን አድርጎ 118 ግቦችን አስቆጥሯል። 

በ2009 የዓለም የተጨዋቾች የዝውውር ዋጋ ክብረ ወሰን በሆነ 94 ሚሊዮን ዩሮ የስፔኑ ሪያል ማድሪድን ተቀላቀለ። በዘጠኝ ዓመት የሪያል ማድሪድ ቆይታውም 438 ጨዋታዎችን አድርጎ 450 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል። አራት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ 16 ዋንጫዎችን ከማድሪድ ጋር አሳክቷል። በሪያል ማድሪድ እያለ በአንድ ዓመት 17 የሻምፒዮንስ ሊግ አጠቃላይ ደግሞ 100 ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ይዟል። 

የማድሪድ ቆይታውን ሲያጠናቅቅም ለሌላ ፈተና ወደ ጣሊያን በማምራት ጁቬንቱስን ተቀላቀለ። ከአሮጊቶቹ ጋር በነበረው የሦስት ዓመታት ቆይታውም ሁለት የስኩዴቶ ዋንጫዎችን አሸንፏል። በክለቡ ታሪክ በአጭር ቆይታ መቶ ግቦችን በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጨዋች ሆኗል።

 

በ2004 በ19 ዓመቱ ከሀገሩ ፓርቱጋል ጋር ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በመድረስ በግሪክ ተሸንፏል። በ2016 ግን ፈረንሳይን በማሸነፍ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። ለሀገሩ 120 ግቦች በላይ በማስቆጠር የምንጊዜም ኢንተርናሽናል ግብ አስቆጣሪ ተጨዋች ነው። 

እስከ አሁን ባለው የአግር ኳስ ሕይወቱ ከዓለም ዋንጫ በስተቀር ያላሸነፈው ዋንጫ የለም። 

አንድ የአውሮፓ ዋንጫ፣ አምስት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ፣ አራት የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ፣ ሦስት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ ሁለት የስፔን ላሊጋ፣ ሁለት የጣሊያን ሴሪ ኤ፣ ሦስት የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ አንድ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ፣ አንድ የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ፣ ሁለት የስፔን ኮፓ ዴል ሬይ፣ አንድ ኮፓ ኢታሊያ፣ ሁለት የካራባኦ ካፕ፣ ሁለት የስፔን ሱፐር ካፕ፣ ሁለት የጣሊያን ሱፐር ካፕ፣ አንድ የእንግሊዝ ኮሚኒቲሺልድ እና አንድ የፖርቹጋል ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሸንፏል።

 

ሦሰት ጊዜ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች፣ አምስት ጊዜ ባሎንዶር፣ አራት ጊዜ የአውሮፓ እግር ኳስ የአመቱ ምርጥ ተጨዋች፣ አራት ጊዜ የአውሮፓ የወርቅ ጫማ (ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር)፣ አንድ ጊዜ የፊፋ ፑሽካሽ አዋርድ፣ ሁለት ጊዜ የጣሊያን ሴሪኤ የዓመቱ ምርጥ፣ ሁለት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ፣ ዘጠኝ ጊዜ የፖርቹጋል የዓመቱ ምርጥ፣ በሁሉም ክለቦች ለ21 ዓመታት የዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ ሦስት ጊዜ የማንቸስተር ዩናይትድ የዓመቱ ምርጥ፣ ሁለት ጊዜ የሪያል ማድሪድ የዓመቱ ምርጥ፣ ሦስት ጊዜ የጁቬንቱስ የዓመቱ ምርጥ፣ አንድ ጊዜ የአል ናስር የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች በመሆን ሽልማቶችን ሰብስቧል። 

40ኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው በ2023 ከተቀላቀለው የሳዑዲው አልናስር ክለብ እየተጫወተ ነው። በዚህ ክለብ ከፍተኛ ተከፋይ ሲሆን፣ ብዙዎች ገንዘብ ፍለጋ ነው ክለቡን የተቀላቀለው ቢሉትም እሱ ግን ይህ ለእግር ኳስ ሕይወቴ አዲስ ፈተና ነው ይላል። የሳዑዲ ሊግም ትልቅ ሊግ እንደሆ ይገልጻል።

ሮናልዶ ከ30 ዓመት በኋላ 460 ግቦችን በማስቆጠርም ከየትኛውም ተጨዋች ይበልጣል። ከ140 በላይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግቦችን በማስቆጠር የሚስተካከለው ተጫዋች የለም። ከ900 በላይ አጠቃላይ ግቦችን በማስቆጠርም አስገራሚ የእግር ኳስ ሕይወቱን ቀጥሏል።

አሰልጣኞች እና ተጨዋቾች ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምን አሉ? 

አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ስለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብቃት በተለያዩ መንገዶች መስክረዋል። ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ያመጡት እና እርሱም እንደ አባት የሚመለከታቸው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፥ "የኔ የምንጊዜም ምርጥ ውሳኔ እርሱን ከስፖርቲንግ ሊዝበን ሳስፈርም ነው፤ እርሱ ማንችስተር ዩናይትድን በአውሮፓ ይበልጥ ትልቅ ያደረገ ሰው ነው" ብለዋል።

በሪያል ማድሪድ ያሰለጠኑት የሀገሩ ልጅ ሆዜ ሞሪኖ “ክርስቲያኖ ሮናልዶን ምትጠላው ከሆነ ወይ ከምትወደው ተጫዋች ይበልጣል ወይም አንድ ቀን የምትደግፈውን ቡድን አፈራርሶታል” በማለት ነው የሚገልጹት። 

በዚያው በሪያል ማድሪድ ያሰለጠነው የቀድሞ ስኬታማ የእግር ኳስ ኮከብ ዚንዲን ዚዳን ደግሞ፣ “ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያንተ ቡድን ውስጥ ካለ ቀድሞውኑ 1-0 እየመራህ ነው” በማለት ስለ ሮናልዶ ምርጥነት መስክሯል። 

በ2008/09 የውድድር ዘመን ባሎንዶርን፣ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋችነትን፣ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን፣ የፊፋ የክለቦች የዓለም ዋንጫዎችን በማሸነፍ በዓመቱ የተዘጋጁ ሁሉንም ሽልማቶችን መጠራረጉን የተመለከተው ፓል ፖግባ ደግሞ፣ “ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ 2008/09 ያደረገውን አንድም ተጫዋች በእግርኳስ ታሪክ አድርጎት አያውቅም” ብሏል። 

የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ጉቲ በበኩሉ፣ "አንድ አስተማሪ በክፍል ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ዝም ማስባል ሊያቅተው ይችላል ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግን 90 ሺህ በአንድ ስታድየም ያሉ ሰዎችን ዝም ሲያስብል አይቻለሁ" በማለት ምስክርነቱን ሰጥቶታል። 

‘አቦ ሸማኔ’ በመባል የሚታወቀው ዩዜን ቦልት፣ "ትራክ ላይ ማንንም አልፈራም ምናልባት ትራክ ላይ ሮናልዶ ቢመጣ እንቀጠቀጣለሁ" ብሏል። 

የቴኒስ ከኮቡ ራፋኤል ናዳል ደግሞ፣ "ሮናልዶን ከሌላ ተጫዋች ምታወዳድር ከሆነ ትክክል አይደለህም፤ ማንቀላፋት ላይ ነህ ማለት ነው፤ ስለዚህ ንቃ!" በማለት ነው ሮናልዶን ከማንም ጋር እንደማያወዳድር የገለጸው። 

የአሁኑ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ እና የባርሴሎና አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ደጋግመው የገጠሙት ፔፕ ጋርዲዮላ፣ "ክርስቲያኖ ሮናልዶ የማይገመት ተጨዋቾች ነው፤ ምንም አቋሙ ቢወርድ እንኳን እኔ ቡድን ላይ ጎል ማግባቱን አያቆምም" ይላሉ። ሚስተር ሻምፒዮንስ ሊግ የሚባሉት ካርሎ አንቼሎቲ ደግሞ፣ "እሱ የምንጊዜም ምርጥ ተጨዋች ነው፤ ምስጋና ለሱ ይሁን እና በአሰልጣኝነት ዘመኔ የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ እንዳጣጥም በእጅጉ ረድቶኛል" ብለዋል።

የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ስኬት ዓላማን ለይቶ በማወቅ፣ ጠንክሮ በመሥራት፣ በራስ በመተማመን፣ ፈተናዎችን በመቋቋም እና በቆራጥነት የመጣ ነው። ከአንዲት የማትታወቅ ትንሽዬ መንደር የተነሳው ልጅ በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ሁሉንም ያሸነፈው ዓላማው ላይ አተኩሮ በመሥራቱ እና ራሱን በመጠበቁ ነው። በዚህም እነ ኪሊያን ምባፔን ጨምሮ ለበርካታ ወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾች አርአያ ሆኗል። 

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top