በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል - አቶ አሕመድ ሽዴ

9 Hrs Ago 32
በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል - አቶ አሕመድ ሽዴ

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ አበክሮ መስራት እንደሚገባው የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አሳሰቡ።

በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የቡድን ሰባት እና የአፍሪካ (G-7 Africa) የሚኒስትሮች ስብሰባ ተደርጓል።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ ተሳትፏል።

ጣልያን በፕሬዝዳንትነት የምትመራው የቡድን ሰባት የፋይናንስ ሚኒስትሮች በእዳ አስተዳዳር ላይ ያሉ ፈተናዎች፣ በአፍሪካ የፋርማሲዩቲካል አምራች ዘርፍ ላይ ያሉ ኢኒሼቲቮች፣ አረንጓዴ መሰረተ ልማት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እና የማይበገር የአቅርቦት ሰንሰለት አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።

በስብሰባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት እየተገበረች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡

ማሻሻያው በግሉ ዘርፍ የሚመራ የኢንቨስትመንት ሽግግር በመፍጠር የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን መፍታት እና የዕድገት ምንጮችን ለማስተካከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ እድገት ያለውን ቁርጠኝነት የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች የአፍሪካ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ከፋይናንስ ተግዳሮት ጋር የተያያዘው የዕዳ መጠን መጨመር፣ የፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ አቅምን በማሳደግ ዙሪያ እና የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ዝርጋታ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ምክክር አድርገዋል።

በመድረኩ ላይ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ፕሬዝዳንት ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና፣ የቡድን ሰባት አባል አገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች መሳተፋቸውን  የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top