"እምቅ አቅም ብቻ ያለን ሳንሆን እንደ ህዝብ ድንቅ ስራ ከውነን ለዓለም ማሳየት የምንችል ህዝቦች ነን" - ቢልለኔ ስዩም

12 Hrs Ago 37
"እምቅ አቅም ብቻ ያለን ሳንሆን እንደ ህዝብ ድንቅ ስራ ከውነን ለዓለም ማሳየት  የምንችል ህዝቦች ነን" - ቢልለኔ ስዩም

ኢትዮጵያውያን እምቅ አቅም ብቻ ያለን ሳንሆን እንደ ህዝብ ድንቅ ስራ ከውነን ለዓለም ማሳየት የምንችል ህዝቦች ነን ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልኡካን ቡድናቸው ከሰሞኑ በማሌዢያ ኳላላምፑር ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ አባል የነበሩት ቢልለኔ ስዩም የማሌዥያ ቆይታቸውን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ በማሌዥያ መዲና ኳላላምፑር የተመለከቷቸው የከተማ ውበቶች በአዲስ አበባ እየተተገበሩ በመሆናቸው ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

የዛሬ አምስት ወር በሲንጋፖር እና በኮርያ ጎዳናዎች ስንቀሳቀስ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ገና በስራ ላይ ነበር ያሉት ኃላፊዋ፤ "ትናንት ማምሻውን ከማሌዥያ ወደ ሀገር ተመልሰን በቅርብ በተሰሩት ጎዳናዎቻችን ላይ ስንጓዝ ከፍተኛ ኩራት በሀገሬ ተሰማኝ" ብለዋል፡፡

በኳላላምፑር ሳለሁ ያየሗቸው ነገሮች እና የኛዋ አዲስ አበባ እየመሰለች የመጣችውን ሳይ ብዙም አላዘንኩም ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ኃላፊዋ፤ እንደ ማሌዥያ ያሉ “Tiger Economies” የሚባሉት ሀገራት በ1980ዎቹ የነበሩባቸው ችግሮች እና ከችግር አወጣጣቸውን ስንመለከት ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ከዛሬ እንደደረሱ እንረዳለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሶስተኛ ትልቅ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን አንስተው፤ ከተሜነት እያደገ በመጣበት ወቅት እኛነታችንን ማሳየት የሚችሉ ትላልቅ ስራዎች ሲሰሩ ልንኮራ ይገባል ሲሉም ገልፀዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top