የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የተጓዥ ሻንጣ እየበረበረ በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ሃሰተኛ ነው - አየር መንገዱ

7 Mons Ago 541
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የተጓዥ ሻንጣ እየበረበረ በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ሃሰተኛ ነው - አየር መንገዱ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትናንት ጀምሮ የአየር መንገዱን ዩኒፎርም የለበሰ ሰራተኛን የራሱን ሻንጣ በማስተካከል ላይ ሳለ የሚያሳይ ምስል ከተሳሳተ መረጃ ጋር በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በመዘዋወር ላይ መሆኑን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ በምስሉ ላይ የሚታየው ግለሰብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ክፍል ባልደረባ መሆኑን እና የአየር መንገዱ ዓርማ የታተመበት ሻንጣም የሰራተኛው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በምስሉ ላይ የሚታየው ቦታ የአውሮፕላን ጥገና ክፍል ባልደረባ የግል ንብረቶች እና ለስራ የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች የሚያስተካክሉበት አካባቢ መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፤ ሌሎቹ ቦርሳዎችም በምስሉ ላይ ያልተካተቱ የሌሎች ባልደረቦች ቦርሳዎች መሆናቸውን ጠቁሟል።

በምስሉ ላይ የሚታየው ስፍራም የመንገደኞች ሻንጣ ሊገኝበት የማይችል እና ለሰራተኞች ብቻ የተከለለ ቦታ መሆኑን የጠቀሰው አየር መንገዱ፤ በተጨማሪም ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት በደህንነት የካሜራ ዕይታ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለክቡራን መንገደኞቹም ሆነ ለንብረቶቻቸው ደህንነት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ እና ሰራኞቹም ደረጃውን የጠበቀ የደንበኛ አገልግሎት ለመስጠት ትጉህ መሆናቸውን አየር መንገዱ አረጋግጧል።

በተሳሳተ መረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስም ለማጥፋት ሆን ተብሎ ኃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች ከሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች ደንበኞች እንዲጠበቁም አየር መንገዱ መልእክቱን አስተላልፏል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top