ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የትራፊክ ፍሠቱን የተሳለጠ ለማድረግ ለኮንስትራክሽን እና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

8 Mons Ago 374
ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የትራፊክ ፍሠቱን የተሳለጠ ለማድረግ ለኮንስትራክሽን እና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የትራፊክ ፍሠቱን የተሳለጠ ለማድረግ እንዲቻል ለኮንስትራክሽን እና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በሃገር ሀብት የተገነቡት እና የተዋቡት የከተማዋ መንገዶች በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደርግ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

በዚህም ችግሩን ለመቅረፍና በተለይም ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የትራፊክ ፍሠቱን የተሳለጠ ለማድረግ እንዲቻል ለኮንስትራክሽን እና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶቾን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ቀደም ሲል በከተማው ላይ በደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎች የተከሰተውን ተመሣሣይ ጥፋት መነሻ አድርጎ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክት ማስተላለፋ ይታወሳል።

አሁንም የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች እና በኦፕሬተር የሚንቀሳቀሱ ማሽኖች ጎማዎቻቸው ሳያፀዱ መንገዶቹን ከማበላሸታቸው ባሻገር ለረጅም ጊዜ በመንገዶቹ ላይ በመቆም እና የሚጭኑትን አሽዋ፣ የቦካ ሲሚንቶ እንዲሁም የግንባታ ግብአቶችን በአግባቡ ሳያስሩ እና ሳይሸፍኑ እያፈሰሱ በመጓዝ በሚፈፅሙት የደንብ መተላለፍ ጥሰት የመንገዶቹ ውበት እየተበላሸ እና የአገልግሎት ዕድሜያቸው እያጠረ መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም የትራፊክ ህግና ደንብን በማስከበር የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ባሻገር ጤናማ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እንዲሁም በመዲናዋ በቀጣይ ቀናት  ለሚካሔደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የፀጥታ አካላት ለሚያከናውኑት የፀጥታ ስራ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር እንዲቻል ከዚህ በታች በተገለፁት መንገዶች ማለትም፡-

  • ቦሌ ድልድይ አካባቢ
  • ከቦሌ ድልድይ እሰከ ሩዋንዳ ድልድይ
  • ከቦሌ ድልድይ በወሎ ሰፈር ደንበል አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ
  • ከመስቀል አደባባይ እስከ አራት ኪሎ
  • ከኡራኤል አደባባይ እስከ አትላስ ሆቴል
  • ከኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል እስከ ልማት ባንከ
  • ከአራት ኪሎ እስከ አምባሳደር መናፈሻ
  • ከብሄራዊ ቴአትር እስከ ሜክሲኮ አደባባይ
  • ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ አፍሪካ ህብረት ትራፊክ መብራት እና
  • ከአፍሪካ ህብረት ትራፊክ መብራት እስከ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ባሉት መንገዶች ላይ ተለዋጭ መረጃ እስኪተላለፍ ድረስ የኮንስትራክሽን ከባድ እና የጭነት ተሽከርካሪንዎችን ማሽከርከርም ሆነ ማቆም የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ አሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እያስገነዘበ ይህንን ተላልፈው በተገኙት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top