ባምላክ ተሰማ የዛሬውን የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ እንዲመራ በካፍ መመደቡ ታወቀ

8 Mons Ago 554
ባምላክ ተሰማ የዛሬውን የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ እንዲመራ በካፍ መመደቡ ታወቀ

ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት እንደሚመራው ታውቋል። 

ካፍ ሞሮኳዊው ሬድዋን ጂይድ ጨዋታውን እንዲዳኙ የመደበ ቢሆንም፣ ዳኛው "የዋንጫውን ጨዋታ መዳኘት ያለብኝ እኔ ነኝ" በማለታቸው ከዛሬው ዳኝነት ተሰርዘው ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል። 

ፌዴሬሽኑ በሞሮኳዊው ሬድዋን ጂይድ ምትክ ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ ጨዋታውን እንዲዳኝ መመደቡን የዘገበው ‘ቢኤስኤን ስፖርትስ’ ነው። 

ምሽት ከ5 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው ጨዋታ የአንድ ጊዜ የዋንጫው ባለድል ደቡብ አፍሪካ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ያሸነፈችውን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ትገጥማለች። 

የደቡብ አፍሪካ ዋና አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ለ3ኛ ደረጃ የሚደረገውን ትግል በድል ለመወጣት ከምንም ነገር በላይ የአዕምሮ ዝግጅት ወሳኝ እንደሆነ ተነናግረዋል። 

ለዋንጫ ለመድረስ የሚችሉትን ትግል ማድረጋቸውን ለካፍ ኦንላይን የገለፁት አሰልጣኙ፣ ዛሬም 3ኛ ደረጃን ይዘን ለማጠናቀቅ የምንችለውን እናደርጋለን ብለዋል። 

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ዲላን ባቱቢንሲካ በበኩሉ፥ በግማሽ ፍፃሜው በአዘጋጇ ኮትዲቯር ተሸንፈው ለፍፃሜ ሳይደርሱ መቅረታቸው የሥነ-ልቦና ጫና ቢኖረውም፤ የዛሬውን ጨዋታ ለክብራቸው እንደሚጫወቱ ተናግሯል። 

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top