ልበ መልካሞቹ የአፍሪካ ኮከቦች

8 Mons Ago 465
ልበ መልካሞቹ የአፍሪካ ኮከቦች

አፍሪካ በቅኝ ግዢዎች ብዝበዛ፣ ከነጻነት በኋላ ደግሞ የራሷ ገዢዎች በፈጠሩባት ጫና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶቿን ልትፈታ አልቻለችም። ይህም ሀብቷ በባእዳን እንዲበዘበዙ ከማድረጉም በላይ ጥሩ ጭንቅላት ያላቸው ልጆቿ የትም እንዲባክኑ አድርጓል። በእግር ኳስም ብንመለከት በአውሮፓ ሊጎች ብዙ ተአምር የሚሰሩ ኮከቦች እያሏት የእግር ኳስ ተሳትፏዋ አመርቂ ሊሆን ያለቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው።   

ከዚህች አህጉር ወጥተው በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ የተለያዩ ኮከብ ተጫዋቾች ከነ ቤተሰባቸው ወደ ተሻለ ህይወት ተሸጋግረው ቅንጡ ህይወት እየኖሩ ነው። የሚያስሩት የእጅ ሰዓት ብቻ የብዙ ምስኪን አፍሪካውያንን ችግሮችን የሚፈታ ዋጋ የሚያወጣ ነው።

አንዳንዶች በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች ትምህርት ቤት ሊያሰራ የሚችሉ ዋጋ ያለው የእጅ ሰዓቶች እና ሌሎች ቅንጡ ቁሳቁሶችን ቢሰበስቡም በችግር ጊዜ ትተውት የሄዱትን ኅብረተሰብ ፈጽሞ አይዘነጉም።

በርግጥም ለፍተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ መልሰው ለህብረተሰቡ የመስጠት ግዴታ ባይኖርባቸውም፣ የወጡበትን ማህበረሰብ ማገዝ ግን የማህበራዊ ኃላፊነታቸው እና የሰው መሆናቸው ዋጋ ነው።

ታዲያ ብዙዎች ቤተሰቦቻቸውን እና ጥቂት ወዳጆቻቸውን ብቻ በመያዝ በአውሮፓ የተንደላቀቀ ኑሮአቸውን ሲቀጥሉ፣ ጥቂቶች የወጡበት ሕዝብ ችግር ችግራቸው ሆኖ በተለያየ መንገድ ሀገራቸውን እየረዱ ለውጥም እያመጡ ነው። በዛሬው ዝግጅታችን ሀገራቸውን በተለያየ መንግድ እየረዱ ያሉ አስር አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በአጭሩ እንመለከታለን።

1. ዲድየር ድሮግባ

ዲድየር ድሮግባ ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ ያደገው ፈረንሳይ ሀገር ነው። ይሁን እንጂ በህጻንነቱ ከማህበረሰቡ ተለይቶ ቢያድግም ማንነቱን አልዘነጋም፡፡ ለሀገሩ እና ለአፍሪካ በመቆርቆር የትኛውም ተጨዋች አይስተካከለውም ይባልለታል።  

ኮትድቯራዊው በእግር ኳስ ሜዳ ለብዙ ግብ ጠባቂዎች አስጨናቂ ቢሆንም፣ በሀገሩ ለሚገኙ በርካታ ሚስኪኖች ግን የደስታ ምንጭ ነው። ድሮግባ ከተለያዩ ሽልማቶች እና ማስታወቂያዎች የሚያገኘውን ገቢ በሙሉ በሀገሩ ለሚገኙ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ይለግሳል። ለምሳሌ ለፔፕሲ በሰራው ማስታወቂያ ያገኘውን 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሀገሩ ሆስፒታል እንዲገነባበት እና በአቢጃን የሚገኙ ወላጅ አልባ ህጻናት እንዲረዱበት አድርጓል። የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ያገኛቸውን ሽልማቶች ሁሉ ለሀገሩ ማኅበራዊ ችግሮች መፍቻ ለግሶአቸዋል፡፡ እሱ የሀገሩ የሰላም ተምሳሌት ነው። ይህን በጎ ተጽዕኖውን በሀገሩ ለአምስት ዓመታት የቆየውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም ተጠቅሞበታል። ድሮግባ በሀገሩ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እና በሌላው የዓለም ክፍሎች ያሉ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት እንደ ዩኒሴፍ ባሉ የተመድ ድርጅቶች ውስጥ በአምበሳደርነት ያገለግላል።

2. ማይክል እሴን

ምርጡ ጋናዊ አማካይ ማይክል እሴን በእግር ኳስ ሜዳ ተቃራኒውን የሚያሸብር ቢሆንም፣ በሀገሩ ለሚገኙ ምስኪኖች ግን ለስላሳ ልብ የለው ያባልለታል። "Michael Essien" የተባለ ፋውንዴሽን አቋቁሞ እንደ ጤና አገልግሎት መሣሪያዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች እና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የመሳሰሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚያስችል ገንዘብ ያሰባስባል። በተማሪዎች ላይ የንባብ ልማድን ለማስረጽ "የንባብ ግቦች" ጨምሮ በበርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይም ይሳተፋል።

3. ጆን ኡታካ

የንስሮቹ እና የእንግሊዙ ፖርትስመዝ የፊት መስመር ተጨዋች የነበረው ኡታካ የናይጄሪያ ወጣቶችን ከመሰረቱ ኮትኩቶ ለማሳደግ "John Utaka" አቋቁሟል። በናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ እርዳታ በዓመቱ የነፃ ትምህርት ዕድል ይሰጣል። ፋውንዴሽኑን ይፋ ሲያደርግም፣ "ወደ ውጭ ሄጄ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ መጫወት ከመጀመሬ በፊት በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ነበርኩ፣ ሁሉንም ነገር ያገኘሁትም ከዚህ ነው፤ ስለዚህ ከህብረተሰቡ ያገኘሁትን መልሼ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ" ብሎ ነበር።

4. አሮን ሞኮኤና

የደቡብ አፍሪካ አምበል የነበረው ሞኮኤና ከእግር ኳስ ክህሎቱ በላይ በሰብአዊ ባህሪያቱ ይታወሳል። በሀገሩ ለተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መመሥረት አስተዋጽ ከማድረጉም በላይ የራሱን በጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም ከፍተኛ ተግባር አከናውኗል። በተጨማሪም በ"አንድ ጎል" እንሺየቲቭ ከሚሳተፉት ተጨዋቾች አንዱ ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜውን እና ገንዘቡን የሚያውለው ለችግረኞች በተለይ ደግሞ ለልጆች ነው።

5. ሳሙኤል ኤቶ

ካሜሩናዊው የፊት መሥመር ተጨዋች በእግር ኳስ ሜዳ የአንበሳ ልብ ያለው ሲሆን፣ ከእግር ኳስ ሜዳ ውጭ ያለው ማህበራዊ ኃላፊነቶቹ ደግሞ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው። በርካታ ነፃ የትምህርት ፕሮግራሞችን አቋቁሞ ብዙ ህጻናት ትምህርት እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን፣ ለጤና ተቋማትም መድኃኒቶችን እና አምቡላንሶችን ለግሷል፡፡ እንዲሁም ሆስፒታሎችን በመገንባት እና የእግር ኳስ ተቋማትን በማቋቋም የሀገሩን ህዝብ ተጠቃሚ አድርጓል። በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ችግረኞችን ለመርዳት በሚደረጉ የበጎ አድራጎት ጨዋታዎች ላይ ተካፍሏል።

6. ሞሐመድ አቡታሪካ

የግብፅ እና አልሃሊ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ሞሐመድ አቡታሪካ በተለያዩ በጎ አድራጎት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ እ.አ.አ በ2005 የUNDP ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮችን የተቀላቀለ ሲሆን፣ 40 ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ኮከቦች ጋር በመተባበር በጀርመን ባከሄዱት 'ድህነት መዋጋት' በሚል የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ተሳትፎ ነበር።

7. ጆን ፓንስቲል

የጥቋቁር ከዋክብቱ ተከላካይ "Paintsil Peace Kids" የተባለ ፕሮጀክት አቋቁሞ ህጻናት ላይ እየሰራ ነው። ፋውንዴሽኑ በልጆች አእምሮ ላይ የአክብሮት እሴቶችን ለመቅረጽ እና ልጆችን ወደ ስኬት መንገድ ለመምራት ያለመ ነው።

8. ኑዋንኮ ካኑ

በጣም ከተወደዱት የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ካኑ በበጎ አድራጎት ሥራዎቹ ይታወቃል። "Kanu Heart Foundation" የተባለ የበጎ አድራጎት ፈውንዴሽን አለው፡፡ የዩኒሴፍ በጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነው ካኑ፣ በልብ እክል ምክንያት ችግር ላይ ያሉ በርካታ ሕፃናትን ወደ ውጭ ልኮ ያሳክማል።

9. ስቴፈን አፒያ

ትሁቱ ጋናዊ የአማካይ ተጨዋች "StepApp" የተሰኘ በራሱ ዲዛይን የሚሰራለት የልብስ ስፌት ተቋም መሥርቷል፡፡ ከዚህ ተቋም የሚገኘው ገቢ በጋና በሚገኙ የተጎዱ አካባቢዎች የጤና ኢንሹራንስ እና የሕክም እና አገልግሎትን የሚውሉ ናቸው። በተጨማሪም በአፍሪካ ትምህርትን ለማስፋፋት በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል።

10. ጆሴፍ ዮቦ

ዮቦ "Joseph Yobo Charity Foundation" በተባለው ፋውንዴሽኑ አማካኝነት በየዓመቱ 300 ለሚሆኑ የመማር አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የትምህርት ዕድል ያመቻቻል። በተጨማሪም በጋና ኦጎኒ በተባለ ክልል የእግር ኳስ አካዳሚ አቋቁሟል። አብዛኛውን የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፈው በበጎ አድራጎት ሥራ ነው።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top