የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ ተጠናቅቋል - የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

279 Days Ago 330
የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ ተጠናቅቋል -  የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ  ባወጣው መግለጫ እንደገለፀው፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገራችን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ ተጠናቅቋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች እና የበዓሉ ታዳሚዎች በየደረጃው ከሚገኙት የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በመሥራታቸው በዓሉ በድምቀት መከበሩም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ባዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ እየተመራ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በማስቀደም ከዋዜማ ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃና እጀባ ተግባራትን በማከናወን በዓሉ እንዲከበር ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ የፀጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላትን አመስግኗል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ ምዕመናን እና የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉ በድምቀት እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ላደረጉት ትብብርና ድጋፍም  ምስጋና አቅርቧል።

በነገው ዕለት የሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓል እንደዛሬው ሁሉ በድምቀት እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም የጋራ ግብረ ኃይሉ  ጥሪ አቅርቧል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ኅብረተሰቡ እስከአሁን ላደረገው ቀና ትብብር ምስጋና አቅርቧል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top