አቶ አረጋ ከበደ የገና በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቀረቡ

9 Mons Ago 335
አቶ አረጋ ከበደ የገና በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቀረቡ

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በክልሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ "የልደት በዓል በመላው ክልላችን በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ በሙሉ ልባዊ ምሥጋናዬን  ለማቅረብ እወዳለሁ" ብለዋል፡፡

በዓሉ በተለይም ደግሞ በታሪካዊቷ እና በደማቋ ላሊበላ ከተማ ያለምንም ችግር እንዲከበር ላደረጉ አካላት በሙሉ ማስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

"ማኅበራዊ ሀብቶቻችን እና ባሕላዊ እሴቶቻችን ለአንድነታችን እና ለጸና መግባባታችን እውንነት ሁነኛ አጋዥ መሳሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሕዝባችን በየአጋጣሚዎቹ ሁሉ የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ ስለመሆኑ በውል ለመረዳት ችያለሁ፤ ለዚህ ገደብ የለሸ አስተዋጽዖም ከልብ ለማድነቅ እና ለማመሥገን እወዳለሁ" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ገና በቅዱስ ላሊበላ እንደተከበረዉ ሁሉ በቀጣይም በክልሉ በሚከበሩ ሌሎች ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት ላይ ቱሪስቶች እንዲገኙ እና በድምቀት በሚከበሩ ኩነቶች ላይ ታዳሚ እንዲሆኑ ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መላው ሕዝብ በዓላቱ በሰላም ይከበሩ ዘንድ ለሚያደርገው አስተዋጽዖ ከወዲሁ ለማመሥገን እወዳለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top