ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ በአባል ሀገራቱ መካከል የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትና የደቡብ ደቡብ ትብብር እንዲጠናከር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ የብሪክስ ሕብረትን በይፋ መቀላቀሏን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ኢትዮጵያ ብሪክስን በይፋ የተቀላቀለችበት የዛሬው ቀን ታሪካዊ ቀን ነው ሲል ገልጿል።
ባሳለፍነው ነሐሴ ወር እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የአጋርነት ሕብረት ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል መወሰኑን መግለጫው አስታውሷል።
ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የምጣኔ ሀብት እድገት በብሪክስ አባልነት እንድትመረጥ ያስቻላት መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ሀገሪቱ በብሪክስ አባልነቷ የደቡብ ደቡብ ትብብር እንዲጠናከር ያላሰለሰ ጥረት እንደምታደርግ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሠላምና ደህንነት እንዲሰፍን እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የበኩሏን ሚና ትጫወታለች ነው ያለው።
እ.ኤ.አ በ2024 የመጀመሪያው ቀን ኢትዮጵያ በይፋ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ ሀገሪቱ በሕብረቱ የሚኖራትን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ ኮሚቴ መቋቋሙንም መግለጫው ይፋ አድርጓል።