ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች ተቀጡ

10 Mons Ago 773
ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች ተቀጡ

የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለቦች ደጋፊዎች በ6ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ላይ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ ክለቦቹ 100 እና 75 ሺህ እንዲቀጡ መወሰኑን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ በ6ኛ ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረበለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በዚሁ መሠረት፥ በተጫዋች ደረጃ ቴዎድሮስ በቀለ ከሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ተስፋዬ መላኩ ከወልቂጤ ከነማ፣ ሞሰስ አዶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ግሩም ሀጎስ ከመቻል በሜዳ ውስጥ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ የ3 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

በክለብ ደረጃ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የውሃ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወደሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቧል።

ደጋፊዎቹ በፈፀሟቸው ሁለት ያልተገቡ ድርጊቶች ክለቡ በድምሩ 75 ሺህ ብር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል።

በተመሳሳይ፥ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም የራሳቸውን ቡድን ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው እና ለመደባደብ ስለመሞከራቸው ሪፖርት ቀርቧል።

የክለቡ ደጋፊዎች በፈፀሙት ድርጊት እና ከዚህ በፊት ከፈፀሙት ስህተት ሊማሩ ባለመቻላቸው የ100 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

በተጨማሪም፥ የመቻል እና የወልቂጤ ከተማ አራት ተጫዋቾች፣ የአዳማ ከተማ አምስት ተጫዋቾች እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ስምንት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበባቸው በመሆኑ ክለቦቹ እያንዳንዳቸው 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ መወሰኑን ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top