የአዲስ አበባ ስታዲየምን የሳር ንጣፍ ሥራ በቅርቡ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ተባለ

11 Mons Ago 258
የአዲስ አበባ ስታዲየምን የሳር ንጣፍ ሥራ በቅርቡ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ተባለ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መመዘኛ መስፈርትን ተከትሎ እድሳት እየተደረገለት ያለውን የአዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ንጣፍ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቸኝነት ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍና ፊፋ የተቀመጠውን መመዘኛ ባለማሟላቱ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ስታዲየሙን ወደ ሥራ ለማስገባት ሰኔ 2013 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ የእድሳት ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ ለእድሳቱ በመንግሥት በኩል 150 ሚሊዮን ብር መመደቡን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን፥ የአዲስ አበባ ስታዲየም የሲቪል ምህንድስና ሥራ ቢጠናቀቅም የሳር ንጣፍ ሥራው እስከ አሁን አለመጀመሩን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በሲቪል ምህንድስናው ብቃታቸው የተረጋገጠ ተቋማትና ባለሙያዎች ቢኖሩም፤ ከሳር ንጣፍ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፈቃድ ያገኘ ድርጅት እንደሌለ ኃላፊው አመልክተዋል።

ይህም የስታዲየሙን የእድሳት ሥራ እንዲጓተት ማድረጉንና ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፥ የሳር ንጣፍ ሥራውን ከፈረንሳይና ከቱርክ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ባለሙያዎችን አምጥቶ ሥራውን ለማከናወን  የዋጋ ጉዳይ ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝና በቅርቡ ሥምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየሙን የእድሳት ሥራ በፍጥነት ለመጨረስ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top