ፍቅር እስከ መቃብር በቅርቡ ይጀምራል

1 Day Ago 97
ፍቅር እስከ መቃብር በቅርቡ ይጀምራል

ፍቅር እስከ መቃብር በቅርቡ ይጀምራል

በፍርድ ቤት የተላለፈው እግድ ተነስቷል

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በአዋጅ የተቋቋመበትን ኅብረተሰቡን የማሳወቅ፣ የማስተማር እና የማዝናናት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ቀጣይነት ባለው የሪፎርም ሥራ ውስጥ ይገኛል።

ለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግሥታቸው ለኢቢሲ ለውጥ በሰጡት ትኩረት ያደገውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ይዘን የይዘት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለንን አዳዲስ የይዘት እና የአቀራረብ ለውጦች እያደረግን እንገኛለን።

የዚሁ አካል የሆነው እና የኢቢሲ የአዲስ ዓመት ስጦታ በሚል ማስተላለፍ የጀመርነው ተወዳጁ ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘው ተከታታይ ፊልም በብዙዎቻችሁ የተወደደ መሆኑን አይተናል።

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ስራ የባለቤትነት መብቱን ጠብቆ ካቆየው ዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ፊልም የመስራት መብቱን በሕጋዊ መንገድ በመግዛት የደራሲውን ክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ሕልም ሊያሳካ በሚያስችል፣ ክብራቸውን እና የተመልካቹን ፍላጎት በጠበቀ መልኩ ከፍተኛ ወጭ በመመደብ ፊልሙ እንዲሠራ አድርገናል።

ይህ እንደ ብሔራዊ ጣቢያ ታሪክ ሰንዶ የማቆየት፣ የማስተላለፍ እና የማሳደግ ሓላፊነታችን ነው። ይህንን የሕግ፣ የሞራል እና ሀገራዊ ሓላፊነታችንን እየተወጣን ባለንበት ወቅት የክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ወራሽ ነኝ በሚሉ ሰዎች የፊልሙን መተላለፍ በፍርድ ቤት እንዲታገድ አድርገዋል።

ኢቢሲ በሕግ የተቋቋመ ሀገራዊ ሓላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የኖረ እና ያለ፤ የደራሲውን ሥራ በወጋየሁ ንጋቱ ትረካ ከፍ ያደረገ እና በዚህም በይፋ ደራሲው ያመሰገኑት ተቋም ነው። አሁንም የተደረገው ያንኑ ሌጋሲ የሚያስቀጥል፣ የደራሲውን ህልም የሚፈታ እና በህጋዊ እና እውቅና ባለው ይሁንታቸው የተላለፈውን መብት መነሻ በማድረግ ፊልሙን ለእይታ አብቅተናል።

ይሁንና አሁን የተከሰተው አይነት ጉዳይ ሲያጋጥም ችግሩን በሕግ አግባብ መፈታት አስፈላጊ በመሆኑ በፍርድ ቤት ስንከራከር ቆይተን እግድ የሰጠው  ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ሲያይ ቆይቶ ህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክርክሩ በስር የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም የተሰጠው እግድ እንዲነሳ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በዚህ መነሻ  በጉጉት ስትጠብቁት የነበረው የፍቅር እስከመቃብር ፊልም በኮርፖሬሽኑ የመዝናኛ ቻናላችን ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጀምር መሆኑን አንገልፃለን።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top