የተቋማት ግንባታ ሥራችን የሀገረ መንግሥት ግንባታው ዋና ምሰሦ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላትን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም፣ ዛሬ መገምገም ተጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤በተቋም ግንባታ ማዕቀፍ በተሠራዉ ሪፎርም በርካታ የሀገር ሀብት ከሚባክንበትና በየዓመቱ ኪሣራ ከሚመዘገብበት ታሪክ መውጣት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ እና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር በየዓመቱ ትርፍ የሚያስመዘግቡ፣ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ለዕውቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ተቋማትን ፈጥረናል ነው ያሉት።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆኑ ሁሉም ተቋማት የተጀመረዉ ሪፎርም ባለፉት ዓመታት የሚለካና የሚቆጠር ውጤት ማምጣታቸውንም አንስተዋል።
በዛሬውመድረክ በዋናነት በመጀመሪያዉ ሩብ የበጀት ዓመት ለማሳካት ካቀድናቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን እንገመግማለን ሲሉም ጠቅሰዋል።
በተገቢው መንገድ ያሳካናቸውን በማየት በጉድለት የታዩትንም በመንቀስ፣ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን በመለየት፣ የጋራ ርብርብ ለማድረግ በቀጣይ ለሚኖረን ምዕራፍ የተሻለ መነሳሳት የምንፈጥርበት መድረክ ይሆናል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።