የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ሲያካሂደው የነበረው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምገማውን አጠናቋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ በክልሉ በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማስፋት ይሰራል ብለዋል።
የማህበረሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ አመራሩ ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት በአገልጋይነት መንፈስን ስራዎችን ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይ በተቋማት ያሉ አደረጃጀቶች እና አሰራሮችን በመፈተሽ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማነቆ የሆኑ የሌብነት፣ ብልሹ አሰራሮች እና የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይባቸውን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ነፃ እና ፍትሀዊ በማድረግ የመልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ እንደሚሰራም አክለዋል።
በሌላ በኩል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡትን አበረታች ውጤቶችን በተሻለ ፍጥነት እና የጥራት ደረጀ እንዲከናወኑ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችም በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተገናኘ ከአምናው የተሻለ አፈፃፀም ቢኖርም በሚፈለገው ልክ አለመሰብሰቡን ገልፀዋል።
በቀጣይ መሰብሰብ እያለባቸው ሳይሰበሰቡ የቀሩ የመንግስት ተሰብሳቢዎች በአግባቡ እንዲሰበሰቡ ትኩረት ሰቶ እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በሩብ ዓመቱ በግብርና ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በተለይ በማሽላ ኢንሼቲቭ የተመዘገው ውጤት እንዲሰፋ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በተለይ በቀጣይ ግዜያት የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት በክልሉ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ዘርፍ ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ውጤታማ ስራ በመስራት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ስራ በማስፋት የማህበረሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ እና በተመረጡ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች የመልሶ ልማት ስራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በክልሉ በክረምት የበጎፈቃድ መርሀ ግብር ማህበረሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።
በተለይ በአረንጓዴ አሻራ 2.5 ሚሊየን ችግኞችን መትከል መቻሉን እና የተሻለ የፅድቀት መጠን መኖሩን በመጠቆም በቀጣይ ስራውን በማስፋት እንደሚሰራ ገልፀዋል።