በአዲስ አበባ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ እና ሳቢ እያደረጓት ይገኛሉ።
የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እንድታስተናግድ ይበልጥ ተመራጭ እያደረጓት ነው።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የክልል ከተሞችም ልምድ እየቀሰሙበት የሚገኝ መልካም ተሞክሮ ነው።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያዬ መርሻዬ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለክልሎች መነቃቃት እንደፈጠረ ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ በመውሰድ በሀዋሳ ከተማም የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በከተማዋ በሦስት ዙር የተጀመሩ ስራዎች ስለመኖራቸው የሚገልጹት ከንቲባው፤ የመጀመሪያ ምዕራፍ 1ኛ ዙር የኮሪደር ልማት ስራው 95 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ሀዋሳን የሚመጥኑ ውብ እና ድንቅ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ከንቲባው፤ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ለክልሎችም መነቃቃት እንደፈጠረ ነው የሚገልጹት።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ተሻገር አዳሙ በበኩላቸው፤ከተማዋን ተጨማሪ ውበት ለማላበስ ይህ የኮሪደር ልማት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኗ አንጻር የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ዋና ዋና ቦታዎችን እንዲያገናኝ ታሰስቦ እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤በመጀመሪያው ዙር የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ በእጅጉ እንደቀየረው ነው የገለጹት።
በከተማዋ ካሉ 11 ክፍለ ከተሞች በ8ቱ የኮሪደር ልማት ስራዎች እንደሚሰሩ አመላክተው፤ የወንዝ ዳርቻ ልማትም በሰፊው ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከተማ ሕይወት እንዳለው ፍጡር ነው፤ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ናቸው።
ለሰው ልጆች የማይመጥኑ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችን አንስቶ ዜጎች ለኑሮ ምቹ በሆኑ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ ማድረጋችን እንደ ስኬት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
በፒያሳ እና በካሳንችስ አካባቢ ለጎርፍ እና ለእሳት አደጋ የተጋለጡ ቤቶችን በማንሳት ዜጎችን ወደ ተሻለ ስፍራ የማዘዋወር ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ይህ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ስራ ክልሎች ትልቅ ተሞክ የሚወሰወዱበት እንደሆነም ጠቁመዋል።