47ኛውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚለየው ምርጫ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ይገኛል

2 Mons Ago 526
47ኛውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚለየው ምርጫ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ይገኛል

ብዙ ውዝግቦች የታዩበት፣ ለምርጫ እጩ የሆኑት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት የግድያ ሙከራዎች የተረፉበትና የዲሞክራት ፓርቲ እጩው ጆ ባይደን እራሳቸውን ከምርጫው በማግለላቸው ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ወደ ምርጫ ፉክክሩ የገቡበት፣ አለምን ብዙ እያነጋገረ የሚገኘው የ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ ሂደት ነገ ፍፃሜውን ያገኛል።

ዶናልድ ትራምፕ እና ተፎካካሪያቸው ካማላ ሀሪስ ከምርጫው ቀን በፊት የመጨረሻ ፉክክራቸውንና ቅስቀሳቸውን ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ካማላ ሃሪስ የዛሬን ቀን ታዋቂ ሰዎችን በመያዝ በፔንስልቬንያ ሲያሳልፉ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ከሰሜን ካሮላይና ጀምሮ በፔንስልቬንያ እና በፒትስበርግ በሦስት ግዛቶች ውስጥ አራት ዘመቻዎችን ለማድረግ ሰለማቀዳቸው ተሰምቷል።

ወደ 77 ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን ቀደም ብለው ድምፃቸውን የሰጡ ቢሆንም ካማላ ሃሪስ እና ትራምፕ በመጨረሻው ቀን ብዙ ሚሊዮን ተጨማሪ ደጋፊዎችን ለማግኘት በሚችሉት ወደፊት እየገፉ ነው።

የእጩዎቹ ፉክክር የዓለም ህዝብን ጨምሮ አሜሪካውያን በምርጫው ቀን የትኛው ታሪካዊ  ውጤት ይመዘገብ ይሆን በሚል በጉጉት እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።

ትራምፕ ካሸነፉ በኒውዮርክ ችሎት ከቀረቡ እና የገንዘብ ቅጣት ከተበየነባቸው በኋላ በመሆኑ በወንጀል የተከሰሱ እና የተፈረደባቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ያደርጋቸዋል።

በሌላ በኩል በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ስልጣን ከያዙት ከግሮቨር ክሊቭላንድ ቀጥሎ ተከታታይ ያልሆኑትን የኋይት ሀውስ ምርጫዎችን በማሸነፍ በታሪክ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት ይሆናሉ።

የ60 ዓመት ጎልማሳ የሆኑት ካማላ ሃሪስ ቢመረጡ እና ወደ ነጩ ቤተመንግስት ቢገቡ የመጀመሪያዋ ሴት፣ የመጀመሪያ ጥቁር ሴት እና የደቡብ እስያ ዝርያ ያለባቸው የመጀመሪያ ሰው ለመሆን ያበቃቸዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የትም ጫፍ ያለን ሀገር በተዘዋዋሪ ወይም በቀጥታ የሚነካ በመሆኑ ከአሜሪካውያን እኩል ወይም በሚበልጥ ደረጃ አለም በጉጉት የምርጫውን ቀን እንዲጠብቀው የሚያስገድድ ሁነት ነው።

ሃሪስ እሁድ ምሽት በሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ዘመቻ “ከመጀመሪያው ጀምሮ ዘመቻችን በአንድ ነገር ላይ መቃወም ሳይሆን ለአንድ ነገር በአንድነት መቆም ነው የሚያስፈልገው“ ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው “አሜሪካን እንደገና ታላቅ እና አንደኛ አናደርጋለን» በማለት መፈክራቸውን አሰምተው፤ በአሜሪካ ለተከሰተው ዋጋ ንረት ዲሞክራቶችን ተወቃሽ አድርገዋል።

በእኔ ጊዜ ኢኮኖሚያችን ወርቃማ ዘመንን እንዲኖረው ለመምራት፣ አለም አቀፍ ግጭቶችን ለማስቆም እና የአሜሪካ ደቡባዊ ድንበርን ለመዝጋት ቃል እገባለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።

ትራምፕ በ2016 ፔንሲልቬንያ፣ ሚቺጋን እና ዊስኮንሲን ግዛቶች አሸንፈው ወደ ነጩ ቤት ቢገቡም በ2020 በሰሜን ካሮላይና፣ ጆርጂያ፣ አሪዞና እና ኔቫዳ ግዛቶች በባይደን ተሸንፈው ስልጣናቸውን አስረክበዋል።

በአሜሪካ ምርጫ 2024 ለምን የፔንስልቬንያ ግዛት በጣም አስፈላጊ የምርጫ ሜዳ ሆነች የብዙዎች ጥያቄ ነው።

በፔንስልቬንያ የሚካሄደው የ19 የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ ሁሌም ወሳኝ ስለመሆኑ ይነሳል።

ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕም ይህንን በመረዳት ይመስላል የምርጫ ቅስቀሳቸውን በአሁኑ ወቅት የተያያዙት በዚህ ቁልፍ ግዛት ውስጥ ነው።

ከ1948 ጀምሮ ማንም የዲሞክራት እጩ ፔንስልቬንያ ሳይመረጥ ፕሬዝደንት መሆን አለመቻሉ ዘንድሮም ለካማላ ሃሪስ በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

በዚህ አጓጊ ምርጫ በአጠቃላይ ከ160 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ድምጽ ይሰጣሉ።

ታዋቂ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በጎራ ተከፍለው ማንን እንደሚደግፉ አስቀድመው ማሳወቃቸው ምርጫውን የበለጠ አጓጊ አድርጎታል።

በዓለማችን የሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ቀድሞ የሚነሳው ኤሎን መስክ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ መሆኑን አስቀድሞ ሲያሳውቅ ቢዮንሴ፣ ጀኒፈር ሎፔዝ፣ ሌዲ ጋጋ፣ ቴይለር ስዊፍት እና ሌሎችም የካማላ ሀሪስ ደጋፊ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ የሚመረጠው እጩ ፕሬዝዳንት ጥር ወር ላይ ስልጣን በይፋ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top