ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለሚጥል እና የተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች ምርመራ የሚውል የሕክምና መሳሪያ ለሆስፒታሎች ለገሱ

1 Day Ago 68
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለሚጥል እና የተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች ምርመራ የሚውል የሕክምና መሳሪያ ለሆስፒታሎች ለገሱ
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው 41 የአዕምሮ ሁኔታን በተለይም የሚጥል በሽታ ለመለየት እና ሌሎች የአዕምሮ ችግሮችን ለመመርመር የሚችል የሕክምና መሳሪያ (ኢኢጂ) ለሆስፒታሎች ለግሰዋል።
 
የሕክምና መሳሪያው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙ 7 ሆስፒታሎች በዛሬው እለት በስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
 
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ከሚሰራቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ የአዕምሮ ጤና ግንዛቤ ማሳደግ፣ ጥራቱንና ተደራሽነቱን የጠበቀ የሕክምና እና ክብካቤ አገልግሎት እንዲሰጥ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መሆኑም ተጠቅሷል።
 
በመሆኑም ጽ/ቤቱ በዚህ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ከዚህ በፊትም ለአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ለጎንደር ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
 
የሕክምና መሳሪያ ድጋፉ ሆስፒታሎቹ እየሰጡ ያለውን የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የተደገፈ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን እንደሚያስችል የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።
 
ድጋፉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የተለያዩ ሆስፒታል ዳይሬክተሮች በተገኙበት ለሆስፒታሎቹ ተበርክቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top