በአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት በታጣቂዎች እና በዘራፊዎች ምክንያት የደፈረሰውን ሰላም ለማስተካከል መንግስት ከህብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥልቅ ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም 151 ሺህ የሚሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶች እና ወጣቶች በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ መክረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በውይይቱ ህብረተሰቡ በዘራፊው ቡድን የሚደርሱ ጉዳቶችን አውግዘዋል ብለዋል፡፡
የዘራፊው ቡድን በሚያደርሰው ጉዳት በክልሉ ያሉ እገታዎች፣ ዝርፊያ፣ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ፣ ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች መስተጓጎል፣ የንግድ ሥርዓቱ መበላሸት እና የስራ አጥ ቁጥር መጨመር የጉዳቱ ውጤቶች ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
በዘራፊው ቡድን ምክንያት የዜጎች ኢኮኖሚም የተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ያነሱት የቢሮ ሃላፊው፣ ይህ ችግር መቆም እንዳለበት ህብረተሰቡ በምሬት ማንሳቱንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ አሁን ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች እንደሚታዩበት ያነሱት የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ በከተሞች ደረጃ 3 ዙር ውይይት መደረጉን እና አሁንም ቀጥሎ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለሰላም እና ለምክክር የሚመጣ አካል ካለ አሁንም መንግስት ዝግጁ ነው ያሉት እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር)፤ ይሁን እንጂ በኃይል መንግስትን ማፍረስ እንደማይቻል የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር መምከሩን አንስተዋል፡፡
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሰላም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሰላም ባለቤት ህዝቡ ነው ያሉት እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር)፤ ህዝቡ ከመከረ የማይስተካከል ነገር የለም ብለዋል፡፡
ዘራፊው ቡድን በሚያደርሰው ሽብር እና ቅሚያ ህብረተሰቡ የማንን ንብረት ነው ምትወስደው? ብሎ ሊጠይቅ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለዘራፊው ቡድን ያለው አቋም ወጣ ገባ ነበር የሚሉት ም/ሀላፊው፤ አሁን ላይ ግን እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ መንግስት አዙሯል ብለዋል፡፡
መንግስት በክልሉ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ እንዲሆን ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን የልማት ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡