ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰላምን በመተመለከተ በሰጡት ምላሽ ዴሞክራሲን በመገንባት ሂደት የሰላም ማጣት ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል፡፡
ሰላም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሰው ለሚያገኘው ጥቅም የማይመጣጠን ዋጋን የማይከፍል አመዛዛኝ ፍጡር ስለሆነ ሰላም ከሁሉም በላይ እንደሚያስፈልገን መዝኖ መያዝ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰላም ግን አንድ ወገን ስለፈለገው ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነ እና ሁሉም ለሰላም ዝግጁ ሆኖ ስለሰላም መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲን በመገንባት ሂደት የኃይል አማራጭ ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሽፍትነት ወደ ሥልጣን የመጣ ቡድን የሀገርን ኢኮኖሚ አሳድጎ እንደማያውቅ የዓለም ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ ለሚፈልገው የሚጨበጥ ዕድገት ሰላም ያስፈልገናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ብናቀርብም ግን በተቃራኒው ያለው ወገን የሚሰጠው ምላሽ ግን ይህን የሚያፈርስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰላም ማጣታችን በዓለም ፊት አንገታችንን እንድንደፋ እያደረገን ስለሆነ መንግሥት ዛሬም ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ አስተውቀዋል፡፡