በተለያዩ ዘርፎች ሲከናወኑ የነበሩ ሪፎርሞችን አጠናቀን ሀገራዊ ማንሰራራት የምንጀምርበት ዘመን የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ተገኝተናል፡፡ በመሆኑም በ2017 በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ የምናስመዘግብ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ከትናንት እሳቤ ወጥተን በጋራ ወደ ነገ መሻገር አለብን፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ተመዝግቧል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመትም 8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ውስጥ ግብርና 6 ነጥብ 1 በመቶ እንደሚያደግ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 30 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
የሌማት ትሩፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ እድገት የተመዘገበበት ዘርፍ ሆኗል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት ምርቶች የ5 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የሚያስመዘግቡ ሲሆን፡፡ ለአብነትም በወተት ብቻ በዓመቱ 12 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት ይጠበቃል፡፡ በዓመቱ 8 ቢሊዮን የዶሮ እንቁላል እንዲሁም 218 ሺህ ቶን ስጋ እና 297 ሺህ ቶን ማር ምርት ለማምረት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡
በቡና ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር 1 ሚሊዮን ኩንታል የምርት እድገት ተመዝግቧል፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ 2ኛ ቡና አምራች ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል፡፡ በተለይ ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የተሻል ስራ የተከናወነ ሲሆን፤ አሁን ላይ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 67 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉም በተያዘው በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ ትልቁን የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይህ አዲስ የሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያም በዓመት ከ100 አስከ 130 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተነናግዳል፡፡ አሁን ላይ 124 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለማግዛት አዘናል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋም ያደርገዋል፡፡ ይህ ለውጥ በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ ለማስመዝገብ የተያዘውን ውስጥ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም የአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡
የኢኮኖሚ ስርዓታችን እጅግ የተዘጋ ነበር፡፡ ይህም በወጪ ንግድ፡ በተኪ ምርቶች፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመት ላይ ኢትዮጵያ መጠቀም ያለባትን ያህል እንዳትጠቀም አድርጓት ቆይቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መሰረት የሚጥል ነው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የመንግስት ገቢ በእጅጉን ጨምሯል፡፡ ባላፉት ሶስት ወራት 180 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ እድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ 109 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት አንጻር አሁንም ዝቅተኛ ገቢ የምትሰበስብ ሀገር ናት፡፡ ይህ በቀጣይ መሻሻል አለበት፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባላፉት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡በዚህ አፈጻጸም ከቀጠልን በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል፡፡ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አለው፡፡ በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በወርቅ ምርት ወጪ ንግድ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም የወርቅ ምርት ምን ያህል ለህገ ወጥ ንግድ ተጋልጦ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ በቡና ምርትም በበጀት ዓመቱ 2 በሊሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ6 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል፡፡በተለይ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ በመፍጠር ረገድ የተከናወኑ ስራዎችም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላት መሬትና ታዳሽ ኃይል፣ እንዲሁም የሰው ሃይል ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ይህን የኢንቨስትመንት አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል መንገድ ከፍቷል፡፡
ባላፉት ሶስት ወራት በተለያየ መንገድ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መጥቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ተመዝግቦበታል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሃብት 400 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው 27 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡
ባላፉት ስድስት ዓመታት መንግስት ምንም አይነት የንግድ ብድር አልወሰደም፡፡ የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከነበረበት ከ30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታትም ይህን አሃዝ ከ10 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግ ይሰራል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት አየር መንገድና ቴሌን ሳይጨምር 13 ቢሊዮን ዶላር እዳ ተከፍሏል፡፡ ይህም እዳን ሳይሆን ለትውልዱ ምንዳን ለማውረስ የምናደርገውን ስራ የሚያግዝ ነው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመፍረስ የታደገ ነው፡፡በሪፎርሙ ባንኩ 900 ቢሊዮን በር የተራዘመ ቦንድ አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስኬታማ መሆን ደግሞ ሁሉንም የሀገር ውስጥ ባንኮች የሚያነቃቃ ነው፡፡አሁን ላይ የባንኮች ተቀማጭ ሃብት 3 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኮች ቁጥርም 32 የደረሰ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ 50 ሚሊዮን ደንበኞች የሞባይል ባንክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት መቅረፍ የምንችለው ምርታማነትን በመጨመር ነው፡፡ የንግድ ስርዓቱን ማዘምንም ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ የኑሮ ውድነቱ እጅ አጠር ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት ከ300 እስከ 400 ቢሊዮን ብር የድጎማ በጀት መድቧል፡፡ ማዕድ ማጋራት፣ ትምህርት ቤት ምገባ እና እሁድ ገበያ መንግስት አቅመ ደካሞችን ለማገዝ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም 249 ሺህ አቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ይህ መንግስት ባለሃብቶችን በማስተባበር ያከናወነው ስራ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ አሁን ላይ ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ይህን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ለ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዟል፡፡ከዚህም ውስጥ 700 ሺህ ለሚሆኑት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ለመፍጠር እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ወራት ለሰለጠኑ ለ100 ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ተፈጥሯል፡፡ ኮዲንግ እና የመረጃ ትንተናን ጨምሮ በርቀት ስራዎች ደግሞ ለ26 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡