"ሰላምን የምንፈልገው ግጭትን ስለምናውቀው እና ህልም ስላለን ጭምር ነው"፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

15 Hrs Ago 26
"ሰላምን የምንፈልገው ግጭትን ስለምናውቀው እና ህልም ስላለን ጭምር ነው"፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ከማንም በላይ ሰላም የምንፈልገው ጦርነትን በተግባር ስለምናውቀው እና ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሰላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ከሃይል አማራጭ ይልቅ የሰላም አማራጭ ተመራጭ ጥቅሙም ብዙ ቢሆንም ሁሉም ሰው አመዛዝኖ ሰላምን ብቻ ስለማይመርጥ "መንግስታት ለዜጎቻቸው መኖሪያ ቤትም ማረሚያ ቤትም" የመገንባታቸውን ምስጢርም ጠቅሰዋል።

መንግስት ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ ሰርቷል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ አሁንም ያለን አቋም የትኛውም አይነት አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ነው ብለዋል፡፡

የትኛውም አካል በኃይል እና ጥላቻ መጠፋፋትን እንጂ ዓላማውን ማሳካት እንደማይችል ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰከን ብሎ ማሳብ እና ሃሳብ አልባ ትግል ፍሬ እንደሌለው መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ለሰላም ካለን ጽኑ እምነት የተነሳ አሁንም እየሰራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ እና ኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ንግግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ እዚህም እዛም ያሉ ሰዎች ሰላምን ሽተው የሚነጋገሩ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር እንዴት ትነጋገራላችሁ እያሉ ጎታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ መንግስት ሰላምን ከሚሹ ሁሉ ጋር ንግግሮችን እያደረገ ሰላምን ለማምጣት የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን ብለዋል።

የመጣንበት የ60 እና 70 ዓመት የፖለቲካ ልምምድ በሃይል፣ በፍረጃ እና ጥላቻ ላይ ተመስርቶ ሲካሄድ መቆየቱ አሁንም ጎታች ሃሳብ መሆኑን አስታውሰዋል።

እንዲህ ያለው ልምምድ ካልተቀየረ በስተቀር ለእኛም ለዓለምም የሚጠቅም አለመሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ "ዓለም ላይ ያለው ልምምድ እንደሚያሳየው በሃይል ወደ ስልጣን የሚመጡ መንግስታት የኢኮኖሚ ለውጥን ማምጣት እና ድህነትን መቀነስ የሚችሉ አለመሆኑን አይተናል" ብለዋል።

“ይህ ስብራት ኢትዮጵያንም በእጅጉ ጎድቷል። ኢትዮጵያን ወደኋላ እንድትቀር ያደረገ ዘመን አሁንም እንድንጓተት ከማድረግ የዘለለ የረባ የሚባል ፋይዳ ስለማያመጣ ሰከን ማለት ይገባል” ብለዋል።

“ለዚህ ነው እኛም ስንመጣ ሁሉንም አብረን እንስራ ብለን ሁሉንም ለማካተት እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንትጋ ብለን የጀመርነው” በማለት አስታውሰዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top