"ዓለም ላይ ተዓምር ካለ ዕፅዋት ተዓምር ናቸው"፡- ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ

3 Mons Ago 876
"ዓለም ላይ ተዓምር ካለ ዕፅዋት ተዓምር ናቸው"፡- ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ

የምርምር ፈር ቀዳጅ እና ፋና ወጊ እንደሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና ተማሪዎቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ ሳይንስ ወደ ህዝብ እንዲደርስ የሠሩ፣ ከሳቸው ጋር የሠሩ ተመራማሪዎች እና ተማሪዎቻቸው ጥናታዊ ጽሑፎችን የማሳተም አቅማቸው እንዲጨምር ያስቻሉ እንደሆነም ይነገርላቸዋል፡፡

ማንኛውንም ሰው በእኩል ዓይን የሚያዩ እና የሁሉም አድማጭ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ የእሳቸውን እርዳታ ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ እና ራሱን ለማሻሻል ጥረት ለሚያደርግ ሰው ሁሉ እጃቸው ሰፊ እንደሆነም ቤተሰቦቻቸው ይመሰክራሉ፡፡

ተማሪዎቻቸውን ሲያስተምሩ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በተግባር በማሳየት ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይገባል። ይሄውም ስለ “ሙጀሌ” ሲያስተምሩ ማሳያ በማጣታቸው ራሳቸውን በሙጀሌ አስበልተው ለተማሪዎቻቸው ማሳየታቸውን፣ "በአንድ ወቅት ሳስተምር የሙጀሌ ናሙና አጣሁ፤ እናም ጫማ አውልቄ ምድጃ አካባቢ እግሬን አኖርኩ፤ ይህንንም ለሦስት ቀናት ሞከርኩ፤ መጨረሻ ላይ ሙጀሌ እግሬ ላይ ወጣች፤ አሳድጌ አውጥቼ ተማሪዎቼን አስተማርኩበት" በማለት ይገልጻሉ።

ስለ ቋንቋዎች መስተጋብር የሚገልጹት "እንግሊዘኛ 15 በመቶ ፈረንሳይኛ ነው፣ አማርኛ 10 በመቶ ዓረብኛ ነው፤ በመሆኑም ሳይንስን ለማለዘብ የውጭ ቋንቋ ብንጠቀም ምንም ችግር የለውም" ይላሉ።

የተፈጥሮ አድናቂ ቢሆኑም እንደ ዕፅዋት የሚያደንቁት ነገር የለም። ይህን አድናቆታቸውንም "ዓለም ላይ ተዓምር ካለ ዕጽዋት ተዓምር ናቸው" በማለት ይገልጻሉ። ይህም ከጸሐይ ብርሃንን ወስደው ምግብ የሚሰሩበትን መንገድ የሚያህል ተዓምር የለም ብለው ማሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ ህዝብ የተረጋጋ እና የተጠና አኗኗር ሊኖረን እንደሚገባ ሲመክሩ ሠርግ በሰማንበት ቤት ሁሉ ከበሮ መደለቅ የለብንም በማለት ነው። ስለ ህዝብ ብዛት ስለሚነገሩ የተዛቡ አስተያየቶች ሲናገሩም ከመጠን በላይ የሆነ የህዝብ ብዛት ካልተጠቀሙበት አሉታዊ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ምዕራባውያን በሚያጋንኑት ልክ እንዳልሆነ፣ ለዚህም ቻይና 1.6 ቢሊዮን ህዝቧን ወደ አምራች ኃይልነት መቀየሯን ያነሳሉ፡፡

በልጅነታቸው የስኬት ጫፍ ነው ብለው የሚያምኑበትን ሽፍታ የመሆን ህልማቸውን ያስጣላቸው ትምህርት የጀመሩት በተወለዱበት አካባቢ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በቢቸና ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፪ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡

አስረኛ ክፍል ሆነው እንደ Thirty-Nine Steps፣ The Brothers Karamazov፣ The Three Musketeers ያሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ አጫጭር ልብ ወለድ መጻሕፍትን ማንበባቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ልብ ወለድ መጻሕፍትን ማንበብ እንደሚወዱ አሁን ግን ከልብ ወለድ ይልቅ የታሪክ መጻሕፍትን፣ ግለ-ታሪኮችን እና የግጥም መድብሎችን ማንበብ ይመርጣሉ፡፡

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፓራሲቶሎጂ ከሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ፣ እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ደግሞ በአኳቲክ ኢኮሎጂ ከካናዳው ዋተርሉ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት የታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ ችግር ነው ብለው ባመኑበት የጥገኛ ተህዋሲያን ላይ ሲሆን፣ የቆሻሻ አወጋገድ ባህል ለነዚህ ተህዋሲያን መራባት ምክንያት እንደሚሆን እና ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ እንደሚገባ የደረሱበት መደምደሚያ ነው፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ የሠሩት በዓሳ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የዓሳ ሀብት ከአያያዝ ጉድለት የተነሳ የሚገባውን ጥቅም እየሰጠ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ዓሳ ሲሰግር ያለ ጊዜው ከሆነ የመጥፋት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነም በጥናታቸው አሳውቀዋል፡፡

የሕይወታቸውን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ በመምህርነት እና በምርምር ሥራ ነው፡፡ "ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፣ የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬ" የሚል የግል ታሪካቸውን በመጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

የተፈጥሮ ሚዛን ካልተጠበቀ ሀገር አደጋ ውስጥ እንደምትገባ የሚያምኑት ፕሮፌሰር ሽብሩ፣ በዚህ ረገድም በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል፡፡ እምቅ የሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ የሆነው የጮቄ ተራራ ተጠብቆ እንዲኖር የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የጮቄ ተራራ ከደረቀ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የምንጠብቀውን ጥቅም እንደማናገኝ የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት እንዲሠሩበት ያሳስባሉ፡፡

ምሑሩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ መኮንን፣ እና ሌሎችም በተለያዩ የሙያ መስኮች ሀገራቸውን ያገለገሉ ምሁራን መምህር የነበሩ ሲሆን፣ የመኢሶን መሥራች ከነበረው ኃይሌ ፊዳ (ዶ/ር) ጋር የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ይደረግ ስለነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲያስታውሱ በደል ቢኖርም ከሀሳብ ፍጭት ውጭ በማንኛውም መንገድ መፍትሔ ያገኛል ብለው እንደማያምኑ እና እንቅስቃሴውን ለመምራት ወደ ፊት የሚወጡ አንዳንድ የዘመኑ ተማሪዎች የሚያደርጓችው ብልጣብልጥነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ልክ እንዳልነበር ይገልጻሉ፡፡

አስተማሪነት እና ተመራማሪነት ቋሚ ተግባራቸው ሲሆን ማንበብ፣ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ክፍል መጎብኘት እና የእግር ጉዞ ማድረግ የሚያስደስቷቸው ልምዶች ናቸው፡፡ በመምህርነት፣ በተማራማሪነት እና በአማካሪነት ብዙዎችን ለከፍተኛ ማዕረግ ያበቁት ፕሮፌሰር ሽብሩ በሙያዊ ሥነ-ምግባራቸው እና በላቀ ተማራማሪነታቸው ልዩነት የፈጠሩ እንደሆነ በብዙዎች ይነገርላቸዋል፡፡

እሳቸውን ለዚህ ከፍተኛ ማዕረግ ያበቃቸው ማንበብ እንደሆነ በማስታወስ አሁን ያለው የሀገራችን የንባብ በህል በጣም እየተሸረሸረ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የንባብ ባህላችንን የጎዳው የማኅበራዊ የትስስር ገጾች መስፋፋት እንደሆነ እና በዚህ መንገድ የሚገኙ መረጃዎችም ለጥልቅ ፍልስፍና እና ምርምር እንደማያበቁ ይናገራሉ፡፡ ያነበበ ትውልድ ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር በመሆኑ ማንበብን ችላ ማለት እንደማይገባም ይመክራሉ፡፡ 

ዕውቀት በምንም ዋጋ የማይተካ መሆኑን ሲገልጹም "የትምህርት ዋጋ የናረ ነው ብለህ ካሰብክ፣ እስኪ መሃይምነትን ሞከረው?" የሚል አባባል ይጠቅሱና ለዕውቀት ማንኛውም ድጎማ ተደርጎ ትውልድን ማዳን እንደሚገባ ነው የሚወተውቱት፡፡

በሥራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶች እና የምሥክር ወረቀቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ሽልማት እና በሳይንስ ዘርፍ የ2010 ዓ.ም የበጎ ሰው ተሸላሚ ናቸው፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top