የ"አረንጓዴ ቀበቶ" ንቅናቄ

2 Days Ago
የ"አረንጓዴ ቀበቶ" ንቅናቄ

በክፍለ ዘመኑ ታዋቂ ከሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች መካከል የ"አረንጓዴ ቀበቶ" ንቅናቄን የመሰረቱት እና በዓለም ዙሪያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአካባቢያዊ እድገት እንዲቆረቆሩ ያነሳሱት ፕሮፌሰር ዋንጋሪ ማታይ ይገኙበታል። 

በአውሮፓውያኑ 1940 በናይሮቢ ኬኒያ የተወለዱት ዋንጋሪ የልጅነት ጊዜያቸውን በኬንያ ገጠራማ አካባቢ አሳልፈዋል። 

በወጣትነታቸው ወደ አሜሪካ በማቅናት በካንሳስ ሴይንት ስኮላስቲካ ኮሌጅ ሥነ-ሕይወት (ባዮሎጂ) ተምረዋል። ከዚያም ከፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂካል ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል። 

ፕሮፌሰር ዋንጋሪ ወደ ኬንያ ተመልሰው በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመከታተል ከማስተማር ባለፈ ለሴቶች መብት የሚታገል የተደራጀ የኬንያ ሴቶች ብሔራዊ ምክር ቤት ንቁ አባል ነበሩ።

 

በአፍሪካ የደን መጨፍጨፍ እና በረሃማነት አብዛኛዎቹ ሴቶች ለምግብ እና ለንጹህ ውሃ የሚተማመኑባቸው ሀብቶች እንዲቀንሱ አድርጓል። 

ታዲያ ጉዳዩን የሰሙት ፕሮፌሰሯ በባዮሎጂ ባላቸው እውቀት እና ሌሎችን ለመርዳት ባላቸው ውስጣዊ ፍላጎት የተነሳ እርምጃ ለመውሰድ ወሰኑ። 

እናም ዋንጋሪ የአካባቢ ሀብቶችን ወደ ነበሩበት መመለስ እና ሴቶች ራሳቸውን ችለው በዘላቂነት ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ማድረግ የሚሉ ግቦችን በመያዝ ወደ ተግባር አቀኑ። 

የፕሮፌሰር ዋንጋሪ እቅድ በ1977 በኬንያ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለድህነት ቅነሳ ለተቋቋመው የ‘ግሪን ቤልት’ ንቅናቄ መሰረት ሆነ። 

ዛሬ ላይ ፕሮፌሰር ዋንጋሪ ማታይ በሕይወት ባይኖሩም በሰሯቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እና በ‘ግሪን ቤልት’ ንቅናቄ ምክንያት በኬንያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታወሱ ይኖራሉ። 

ዋንጋሪ "ተነሳና ሂድ" በሚለው ታዋቂ ንግግራቸው እያንዳንዳችን የምናወጣውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ለማካካስ 10 ዛፎችን በመትከል መጀመር እንደምንችል አስተምረዋል። 

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት መዛግብት ያሳያሉ። የነበረው ዘላቂ ያልሆነ የመሬት አጠቃቀምና የተፈጥሮ ሁኔታ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ አውርዶት ነበር። 

ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን በዘላቂነት ለመስራት፣ በረሀማነትን ለመቀነስ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከ5 ዓመታት በፊት ነበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን የጀመረችው። 

በዚህ መርሀ ግብር ባለፉት 5 ዓመታት 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ሲተከሉ፤ ከ20 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንም በተከላው ተሳትፈዋል። 

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ አድጓል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top