ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

4 Days Ago
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ እያደረጉት ያለው የስራ ጉብኝት በዩጋንዳ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም እና የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የመጀመሪያ ልጅ በሆኑት ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በተደረገላቸው ግብዣ ነው፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የልዑካን ቡድናቸው ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዩጋንዳ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በዩጋንዳ ምድር ኃይል ኮማንደር ሌተናል ጄኔራል ካያንጃ ሙሃንጋ፣ በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ይመኑ እና በሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ፊልድ ማርሻሉ በቆይታቸው ከዩጋንዳ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ጋር በሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ዘርፍ ትብብር እና ሀገራቱ በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ በማስፈን ረገድ እያደረጉት ያለውን ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተጠናከረው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በቀጠናው ሰላምና ጸጥታን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩጋንዳ የጦር ሀይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በበኩላቸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ በታሪክና በደም የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በተናጠልም ሆነ በጋራ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የተሻለ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚቻልበት ሁኔታን የዳሰሰ ሲሆን በአቅም ግንባታና ተጨማሪ ትብብሮችን አስመልክቶ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ኢቢሲ ከልዑካን ቡድኑ የደረሠው መረጃ እንደሚያመላክተው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በነገው እለት ከዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top