በጠፋ የኤቲኤም ካርድ የወጣው ገንዘብ

3 Days Ago
በጠፋ የኤቲኤም ካርድ የወጣው ገንዘብ

ዘመናዊ አኗኗር ጥሬ ገንዘብ አልባ ነው። ‘‘ገንዘብ አልባ አይደለም ያልኩት’’ ገንዘቡን በብር በሳንቲም ይዞ ከመዘዋወር የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባስገኛቸው በረከቶች የሚጠቀም ማለቴ ነው። የዘመኑ ግብይት በጥሬ ሳይሆን በካርድ፣ በኢንተርኔት፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በዲጂታል ባንክና በሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀሻ በኩል እየሆነ መጥቷል።

 

በእነዚህ ዘመናዊ የሂሳብ ቋት ማንቀሳቀሻ ዘዴዎች በፍጥነት ጥሬ ገንዘብ ማውጣት፣ ከራስ ሂሳብ ቋት ወደ ሌላ ሰው ሂሳብ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ክፍያዎችን መፈፀም ተችሏል።

 

እነኚህ ቴክኖሎጂዎች የወረቀት ገንዘብን እየተኩ ነው። ከዘረፋም ከድካምም የሚያድኑ ሲሆን ፍጥነትና ቅልጥፍናንም ይጨምራሉ።

 

ቀደምቶቻችን የአሞሌ ጨው፣ የጥይት ቀለሀ፣ ማርትሬዛ ፣የብር ገንዘብ ሳንቲሞችና የወረቀት ብሮች የገንዘብን ኃያል ጉልበት እንደያዙ ሲገበያዩባቸው ኖረዋል። አሁን በኛ ትውልድ የዲጂታል የክፍያ ዘዴዎች ላይ ደርሰናል።

 

ከእነዚህ የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ጋር በባንኮችና በደንበኞቻቸው መሀከል አከራካሪ የሕ ጉዳዮች መነሳታቸው አልቀረም። እስቲ ከኤቲኤም ካርድ ጋር በተያያዘ በአንድ ባንክና በደንበኛው መሀል የተነሳ የፍርድ ቤት ክርክር እና የመጨረሻውን አስገዳጅ ውሳኔ እንመልከት።

 

የኤቲኤም ካርዳችሁ ጠፍቶ ለባንኩ ካሳወቃችሁ በኋላ ከሂሳባችሁ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ ቢገኝ ተጠያቂው ማን ነው? እስቲ ግምታችሁን አስተያየት መስጫው ላይ አጋሩን።

 

ይሄ ጉዳይ በአንድ ባንክ እና በደምበኛው በአቶ አበባየሁ መሀል ተነስቶ ነበር። አቶ አበባየሁ በባንኩ ያላቸውን የሂሳብ ቋት በኤቲኤም ካርድም ለማንቀሳቀስ ተስማምተው ከባንኩ ካርድ ወስደው ሲጠቀሙበት ቆዩ። ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም ኤቲኤም ካርዱ ይጠፋባቸውና አፈላልገው ስላላገኙት ጥር 25 ቀን ለባንኩ በፅሁፍ ካርዳቸው መጥፋቱን አሳወቁ።

 

አቶ አበባየሁ ለባንኩ አሳውቄያለሁ አገር አማን ነው ብለው በተቀመጡበት ለካ ከባንክ የሂሳብ ቋታቸው ገንዘብ እየታለበ ኖሯል። ካርዱ መጥፋቱን ለባንኩ ካሳወቁበት ከጥር 25 ጀምሮ እሰከ የካቲት 6 ባሉት 11 ቀናት 40, 300 ብር ማንነቱ ባልታወቀ ሰው በኤቲኤም ካርዳቸው ወጪ ተደርጓል።

 

አቶ አበባየሁ ይሄን ሁኔታ ለባንኩ አሳወቁ። መፍትሄ አልሰጣቸውም። ከሰሱ። በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ባንኩ እንደጠፋብኝ ባሳወቁት የኤቲኤም ካርድ ወጭ የተደረገውን 40,300 ብር ከነወለዱና ለክሱ ካወጣሁት ወጪና ኪሳራ ጋር ይክፈለኝ ብለው ለባንኩ መጥሪያ አደረሱት።

 

ባንኩ ምን ቢል ጥሩ ነው? አዎ ካርዱ መጥፋቱን አሳውቀውኛል። ግን በአሠራሬ መሰረት የሂሳብ ቋታቸው ይዘጋ ብለው ስላልጠየቁ የሂሳብ ቋታቸውን አልዘጋሁትም። ስለዚህ ገንዘቡ ወጪ ተደርጓል ግን የሚስጥር ቁጥራቸውን ከሳሽ ካልነገሩ ማንም ሊያውቀው ስለማይችል እና የሂሳብ ቋቱ እንዲዘጋ ስላልጠየቁ ለገንዘቡ በኃላፊነት መጠየቅ የለብኝም አለ።

ፍርድ ቤቱም የአቶ አበባየሁን እና የባንኩን ሙግት መረመረ። ከሳሽና ተከሳሽ በገቡት በኤቲኤም ካርድ የሂሳብ ቋትን የማንቀሳቀስ ውል ላይ ካርዱ መጥፋቱን ደንበኛው በፅሁፍ ለባንኩ ከማሳወቁ በፊት ለተደረገ ክፍያ ሁሉ ባለካርዱ ኃላፊ ነው ይላል።

 

ፍ/ቤቱም ካርዱ ከጠፋና ደንበኛው ለባንኩ ካሳወቀ በኋላ ገንዘብ ወጪ ቢደረግ? ለሚለው የከሳሽ ጥያቄ አፅንኦት በመስጠት በተቃርኖ የውል አተረጓጎም መርህ መሰረት ይህ አባባል ሲተረጎም የባንኩ ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዝባል ሲል ወሰነ።

 

ሌሎች ነጥቦችንም ፍርድ ቤቱ አነሳ። የመጀመሪያው ነጥብ በውሉ ላይ ባንኩ ኃላፊነት ሚወስደው ደንበኛው የጠፋበት የኤቲኤም ካርድ ሂሳብ እንዲዘጋ ሲያመለክት መሆኑን ሚገልፅ ነገር አለመኖሩ ነው።

 

ሁለተኛው ደንበኛው የኤቲኤም ካርዱ መጥፋቱን ሲያመለክት የሚስጥር ቁጥሩን ባንኩ ባዘጋጀው ፎርም ላይ መፃፉን ባንኩም በማመኑ ሠራተኞቹ የሚስጥር ቁጥሩን ሊያውቁ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ጠቀሰ። በነዚህ ምክንያቶችም የባንኩ መከራከሪያ ነጥቦች ተቀባይነት የላቸውም ብሎ ባንኩ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍል ተወሰነበት።

 

ባንኩ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም አልተሳካለትም።

 

በመሆኑም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ሲል የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

 

የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ውሳኔ ሰጠ። አምስት ዳኞች በተሠየሙበት ችሎት መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም በሰ.መ.ቁ 96309 ላይ ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ ነው ተሰጥቷል።

 

‘‘የሚስጥር ቁጥሩን አቶ አበባየው በስህተት እንኳን ቢፅፉ ፎርሙ መቀመጥ አልነበረበትም። ባንኩ የተለመደውን ጥንቃቄ ማድረጉን እና ጥፋት አለመሥራቱን ማሳየት ይጠበቅበት ነበር ሆኖም አላሳየም። ደንበኛው ሂሳቡ እንዲዘጋ አልጠየቁም በሚል ምክንያትም ባንኩ ከኃላፊነት አይድንም ። በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት ስለሌለ አፅንቼዋለሁ’’ ብሎ ወሰነ። (ውሳኔው የሰበር ፍርዶች ቅፅ 17 ላይ ይገኛል)

 

የኤቲኤም የካርድም ሆነ ሌሎች ዘመናዊ የባንክ ሂሳብ ማንቀሳቀሻ አማራጮችን የባንክ የሂሳብ ቋትን ለማንቀሳቀስ ደንበኞች ከአገልግሎት ሰጪ ጋር የሚገቡትን ውል ላይ ያሉ መብትና ግዴታዎቻቸውን ማወቅና ባንኩም የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጥበቃ መመሪያ በሚያዘው መሠረት ማሳወቅ አለበት።

 

የባንክ ደንበኞችም የሂሳብ ቋታቸውን የሚያንቀሳቅሱባቸውን አማራጭ ዘዴዎች ሲጠቀሙ የሚስጥር ቁጥራቸውን ለሌላ ሰው ለባንኩ ሠራተኛም ቢሆን አለመስጠት፣ ካርድ ወይም ስልካቸው እንዳይጠፋ በጥንቃቄ መያዝ፣ ከጠፋም ወዲያውኑ በተለያዩ የማሳወቂያ መንገዶች ለባንኩ ማሳወቅ አለባቸው።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top