የአከራይ እና ተከራይ ሕጋዊ ውል ምዝገባ በነዋሪዎች እንዴት ይታያል?

3 Days Ago
የአከራይ እና ተከራይ ሕጋዊ ውል ምዝገባ  በነዋሪዎች እንዴት ይታያል?
የግል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ 13220/2016 መሰረት የአከራይ እና ተከራይ ሕጋዊ ውል ምዝገባ እየተካሄደ ነው።
 
ምዝገባው ከተጀመረ ጀምሮ በቀን በአማካይ ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
 
ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ የነበራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነት ወ/ሮ ሂሩት ከበደ አከራይም ጭምር ናቸው።
 
የአከራይ እና ተከራይ ምዝገባን በተመለከተ “ጥቅም እንዳለው ማወቅ አሁን አይቻልም ግን ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል እጠብቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
 
በተለይ ብዙ ጊዜ የሚስተዋለውን የአከራይ እና ተከራይ ጭቅጭቅ ለማስቀረት እና በሕጋዊ መንገድ ስምምነት ለማድረግ ጠቃሚ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
 
አከራይ ያለ ወቅቱ ተከራዩን ከማስወጣት፣ ያለ አግባቡ ገንዘብ ከመጨመር እንዲሁም ለደላሎች በየጊዜው ገንዘብ ከመክፈል እና ከመንገላታት እንደሚታደግ አንስተዋል፡፡
 
በከተማው ብዙ ሰው ተከራይቶ ነው የሚኖረው የሚሉት በአዲስ አበባ ቤት ተከራይተው የሚኖሩት አቶ ያረጋል ጫን ያለው፤ ተከራይ በየሥድስት ወሩ ቤት በመቀየር ለእንግልት እና ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገናል ነው ያሉት።
 
እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ሕጋዊ ሥርዓት እንዲኖር መደረጉ ለተከራይ አንድ እረፍት ነው የሚሉት አቶ ያረጋል፤ በሕገ ወጥ ደላሎች ከሚደርስ ውጪ እና እንግልት የሚታደግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
አቶ ሰለሞን ሞገስ ግን እንዲህ ያለ ሕግ መውጣቱ በተለይ የአከራዩን መብት የሚጋፋ ይሆናል ባይ ናቸው። ሰዎች ቤት ሲሰሩ ለፍተው እና መተዳደሪያዬ ነው ብለው የሰሩትን ቤት ባልፈለጉት መልኩ በውዴታ ሳይሆን በግዴታ እንዲያከራዩ ሊያደርግ ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው።
 
ይህም የቤት ባለቤት የሆነ ሰው በቤቱ የማዘዝ ሙሉ መብቱን ይጋፋል የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ አከራዩ ላይ ጫና ይፈጥራል ነገር ግን ይህን በሚያጣጥም መልኩ ከተተገበረ የሚጠቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ፈይሳ "በቀን ከ11 ሺህ በላይ የአከራይ እና ተከራይ ውል ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑ በመጥቀስ፤ ይህም የአከራይ እና የተከራይን መሰረታዊ መብቶችን በጠበቀ መልኩ የሚተገበር እንደሆነ ነው የገለጹት።
 
በአዋጁ እና በመመሪያው መሰረት እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ምዝገባ፤ አከራይ ውል ማፍረስ የሚችልበት ሁኔታ የለም ያሉ ሲሆን ነገር ግን መመሪያው ላይ ተከራይ ግዴታ የሚጣልበት ነገር ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
 
አከራይ ውል ለማፍረስ ከሥነ-ምግባር ችግር፣ የወር ኪራይ ካለመክፈል ፣ተከራዩ ቤቱን ያለአከራዩ ፈቃድ ከመኖሪያነት ውጪ ወይም ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ከሆነ እና መሰል ጥፋቶች ጋር በተያያዘ እና ከተረጋገጠ ካልሆነ በስተቀር በራሱ ተነሳሽነት ውል ማፍረስ አይችልም ብለዋል ኃላፊው፡፡
 
አሁን እየሆነ ያለው ሁለት መብት ያላቸውን አካላት አስማምቶ ማስተሳሰር ነው ያሉት ኃላፊው፤ አከራይ ቤቱን ማደስ እና መሰል ነገሮችን ቢፈልግ በውሉ ላይ በተቀመጠው ጊዜ ውሉ በሚያበቃልበት ወቅት ማድረግ እንደሚችል አንስተዋል።
 
አከራይም ሆነ ተከራይ ምዝገባ ከተጠናቀቀ እስከ 3 ወር ድረስ የሚመዘገቡ ከሆነ የዘገየው ማን እንደሆ ተጣርቶ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ቅጣት እንደሚከፍል ተናግረዋል።
 
ከ3 ወር በኋላ የአከራይ ተከራይ ውል ለማድረግ የሚመጣ ደግሞ የሁለት ወር የቤት ኪራይ እንደሚቀጣ መደንገጉን ገልጸዋል።
 
ይሁን እንጂ ይህን ውል ሳይፈጽሙ ወይም ተደብቀው በተቆጣጣሪ አካል የተገኙትን ደግሞ እስከ 3 ወር የቤት ኪራይ ቅጣት ይጣልባቸዋል ነው ያሉት።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top