በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖሎች የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ያሳዩ ናቸው - አቶ መላኩ አለበል

3 Mons Ago 615
በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖሎች የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ያሳዩ ናቸው - አቶ መላኩ አለበል

በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖሎች የሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያሳዩ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥ እንደተመረቱ ተናግረዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አቅም በማጎልበት ከውጭ የሚገባ ምርትን በአገር ውስጥ መተካት እንደሚቻል ያመላከተ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የኢትዮጵያ አምራች ዘርፍ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተሰጠው ትኩረት ምርታማነቱ እና በገበያ ውስጥ ያለው ድርሻ ፈጣን እምርታ እያሳየ መጥቷል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መጀመራቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

ለአብነትም በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ ስማርት ፖሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጭነት ምርቱ በሀገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ወራት በፊት መመረት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የስማርት ሲቲ የኤሌክትሪክ ፖል ከአምሰት ያላነሱ ንዑሳን ክፍሎች እንዳሉት ገልፀው፤  ይህን ፖል በአንድ ፋብሪካ ብቻ ለማምረት ቴክኖሎጂና ፋሲሊቲ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የሀገር ውስጥ አምራች ፋብሪካዎች በጋራ በመሆን የጋራ ዲዛይን ሰርተው በትብብር ወደ ማምረት  ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምና የቴክኖሎጂ ሽግግር የታየበት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፋብሪካዎቹ በቀን ከአንድ ፖል ወደ 26 ፖል የማምረት አቅም በማሳደግ የማምረት ፍጥነትና የአመራረት ስርዓት ባህል ያሳደጉበት አጋጣሚ እንደሆነ አንስተዋል።

ከዚህ ባሻገር በስማርት ኤሌክትሪክ ፖል ምርት 673 ቋሚ የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን አምራቾች ከ370 ሚሊዮን በላይ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏልም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የተተከሉ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖሎች ከሀገር ውስጥ ከተሞች ባሻገር ሌሎች አፍሪካ ከተሞችም ከኢትዮጵያ ተሞክሮ የሚወስዱበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የስማርት ኤሌክትሪክ ፖል ምርት ፋብሪካዎች ግብዓት ተመጋግበው ወጥ ምርት ያመረቱበት ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ከማስገኘቱ ባለፈ  የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የስማርት ኤሌክትሪክ ፖልን ጨምሮ አምራች ዘርፉ ምርታማ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉንም ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top