ደቡብ አፍሪካውያንን ከቂም በቀል መንገድ የመለሳቸው የምክክር ሒደት እንዴት ተሳካ?

23 Days Ago
ደቡብ አፍሪካውያንን ከቂም በቀል መንገድ የመለሳቸው የምክክር ሒደት እንዴት ተሳካ?

እ.አ.አ. ታህሳስ 20 ቀን 1991 የዲሞክራሲያዊ ደቡብ አፍሪካ ኮንቬንሽን (ኮዴሳ) የመጀመሪያ ምልአተ ጉባኤ በኬፕተዎን ፓርክ ውስጥ በሚገኘው የዓለም ንግድ ማዕከል ተካሄደ። ይህ የምክክር ጅማሮ ሀገሪቱን ከአፓርታይድ ሥርዓት ነፃ ለመውጣት እና ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደትን ለመፍጠር ያለመ ነበር።

ለ46 ዓመታት ያህል የዘለቀው የአፓርታይድ አገዛዝ በደቡብ አፍሪካውያን ላይ ጥቁር አሻራን ያሳረፈ ሥርዓት ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት ኔልሰን ማንዴላ እና አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞች ከሮበን ደሴት እስር ቤት መልቀቃቸውን ተከትሎ የአፓርታይድ ሥርዓትን ለማስወገድ በ1990 ድርድር ተጀመረ። 

ደ ክለርክ የተሰኙት የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የአፓርታይድ ሥርዓት መሐንዲስ የፈጠረው የብሔራዊ ፓርቲ መሪ ነበሩ። እሳቸው የአፓርታይድ ሥርዓትን በማስወገድ የምክክር ሂደት የሚጀመርበትን ምቹ ሁኔታ በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራቸው።

ታዲያ ይህን የአፓርታይድ ሥርዓት ለማስወገድ የኮዴሳ ድርድር እና ሌሎች ምክክሮች አልጋ በአልጋ የሄዱ አልነበሩም። በአፖርታይድ ሥርዓቱ ደቡብ አፍሪካ ክፉኛ ቆስላለች፤ ቂም በቀል እና መሰል ስሜቶች ከፍ ያሉበት ጊዜ ነበርና ከደም መፋሰስ ወደ ሌላ እልቂት ላለመሸጋገር ስሜትን ገርቶ ቁጭ ብሎ መምከር አስፈላጊ ነበር።

ሥርዓቱን ሲታገሉ የነበሩት ያለሟት አዲስ ዲሞክራሲያዊ ደቡብ አፍሪካ መሠረቶች፣ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች፣ ጊዜያዊ የመንግሥት አደረጃጀት እና የተከፋፈሉት የአገሪቷ ግዛቶች ቀጣይ እጣ ፋንታ የምክክሩ ማጠንጠኛዎች ነበሩ።

በወቅቱ አብዛኞቹ የምክክሩ ተሳታፊዎች የተባበረች ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካ የምትመሰረትበትን የሚደግፉ ሀሳቦችን ያነሱ ነበር እና ነገሮች በጥሩ መስመር ላይ ያሉ መስለው ነበር።. ከአንድ ዓመት በኋላ ግን በግንቦት 1992 በሥልጣን መጋራት እና በአብላጫ ደንብ ላይ በተነሱ ክርክሮች ምክንያት ድርድሩ ተበተነ። በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የታወቀው የቦይፓቶንግ እልቂትን ጨምሮ ከባድ ትርምሶች ተፈጠሩ።

ይህም አስቸኳይ ምክክሮች አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው እና ሰላማዊ ውሳኔ ላይ መድረስ አማራጭ የሌለው እና ደቡብ አፍሪካውያንን ተጨማሪ ስቃይ ውሰጥ ሳይገቡ በይቅርታ ለማሻገር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አሳይቷል።

በ1993 በኬምፕተን ፓርክ የብዝሀ ፓርቲ የምክክር መድረኮች የቀጠሉ ሲሆን፣ በሚያዝያ ወር ደግሞ ተደራዳሪዎች በሽግግር ሒደቱ አቅጣጫዎች ላይ ተስማምተዋል። ይህን የምክክር ሂደት ያልደገፉ ጥቂት ፓርቲዎች እንዲደናቀፍ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም ለምርጫ መንገድ የሚከፍት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በምክክሩ ብሔራዊ ፓርቲ የአናሳ ነጮች የመብት ጥያቄዎችን እና የሥልጣን መጋራት የሽግግር ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት እንዲመሠረት ተስማምተዋል።  በኅዳር 1993 የመድብለ ፓርቲ ምክክር መድረክ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት ምርጫን ሕጋዊ የሚያደርግ ጊዜያዊ ሕገ መንግሥትንም ማፅደቅ ችሏል።

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1994 ደቡብ አፍሪካ ለሁለት ቀናት ሰላማዊ ምርጫ አካሂዳለች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ምርጫ ድምጽ ሰጥተዋል።  ኤ.ኤን.ሲ ከዌስተርን ኬፕ እና ክዋዙሉ ናታል በስተቀር ሁሉንም ግዛቶች በማሸነፍ አስደናቂ ድል ማግኘት የቻለ ሲሆን ሕገ መንግሥቱን በራሱ እንደገና ለማሻሻል ሁለት ሶስተኛውን ድምጽ ማግኘት አልቻለም።

እ.ኤ.አ. ከ1948 እስከ 1989 ሰፍኖ በነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ሺዎች በጨለማ ክፍል ማቅቀዋል ሚሊዮኖችም ተሰድደዋል። ይህን እጅግ አሰቃቂ ሥርዓት የጣሉት ደቡብ አፍሪካውያን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ከቂም በቀል እርምጃዎች ይልቅ ሰላም እና ፍትህን መረጡ። በመሠረቱት የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን ያን ፈታኝ ወቅት አልፈው ዛሬ ላይ በአህጉሪቱ ብሎም በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል።

ኢትዮጵያዊያንም በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች፣ ትርክቶች እና ያደሩ ቁርሾዎች ያለያዩአቸውን ጉዳዮች መክረው ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን ተቋቁሞ በሂደት ላይ ይገኛሉ።

ታዲያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሊገጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን ከሌሎች ሀገራት በመማር ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባው ይነሳል።

ሰለሞን ከበደ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top