ስኬታማው የቻይና የመጸዳጃ ቤት አብዮት

1 Mon Ago
ስኬታማው የቻይና የመጸዳጃ ቤት አብዮት

መረጃዎች እንደሚያሳዩት እ.አ.አ ከ2015 በፊት የቻይና የመጸዳጃ ባህል የሀገሪቱን ታሪክ እና የዕድገት ደረጃ የማይመጥን ነበር፡፡ በሁሉም የገጠር የሀገሪቱ ክፍል እና በአብዛኛው ከተሞቿ በሚባል ደረጃ መንገድ ዳር መጸዳዳት እና የመጸዳጃ ፍሳሽን በየአካባቢው መልቀቅ የተለመዱ ነበሩ፡፡

እ.አ.አ በ1993 ከቻይና የገጠር ነዋሪዎች መካከል ከ8 በመቶ ያነሱት ብቻ ነበሩ መጸዳጃ ቤቶችን የነበራቸው። የመጸዳጃ አብዮት በሚታወጅበት ዋዜማ በ2014 ይህ ቁጥር ተሻሽሎ የነበረ ቢሆንም የነበሩት መጸዳጃ ቤቶች እና የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ ከደረጃ በታች ስለነበሩ አካባቢን የሚበክሉ ፍሳሾችን እና መጥፎ ጠረኖችን ማየት የተለመዱ ነበሩ።

በዚህም ምክንያት እንደ ተቅማጥ፣ ኮሌራ፣ የወባ በሽታ እና ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎች ቻይናን ይፈታተኑ እንደነበር ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ሁኔታ ቻይና በኢኮኖሚ ዕድገት ተፎካካሪ እየሆነችበት ያለውን ነበራዊ የዓለም ሁኔታ የማይመጥን መሆኑን ነው መሪዎቿ የተገነዘቡት፡፡

                                   

ቻይና በሁሉም ረገድ ተፎካካሪ እንድትሆን ያስቻሉት ፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ቆርጠው ተነሱ፡፡ ቻይና ስሟን የሚመጥን ንጽህና እንዲኖራት "የመጸዳጃ ቤት አብዮት" አወጁ፡፡ ቻይናውያን ክብራቸውን የሚመጥን መጸዳጃ ቤት እንዲኖራቸው እና ሀገራቸው በውጭ ጎብኚዎች ዘንድ ጥሩ ምስል እንዲኖራት ወስነው የተነሱት ፕሬዚዳንቱ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ንቅናቄ ፈጥረው የተሳካ ሥራ ሠርተዋል፡፡

ምቹ ያልሆኑ እና የቆሸሹ የመጸዳጃ ቦታዎችን በማስተካከል፣ ንጽህናቸውን የጠበቁ እንዲሁም ምቹ የሆኑ የመጸዳጃ ፋሲሊቲዎችን ማብዛት የሚለው የፕሬዚዳንቱ መርህ ነበር። የመሪ ፖለቲካዊ ውሳኔ ቻይና በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ትልቁን እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የባቡር ቴክኖሎጂ እንድትፈጥር እንደረዳት የሚያውቁት ፕሬዚዳንት ዢ በመጸዳጃ ቤቶች አብዮቱም ተመሳሳይ አቋም መውሰድ ግድ እንደሚል ወስነው ነው ወደ ሥራ የገቡት።

በቻይና በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል በየቦታው መጸዳዳት የተለመደ ነበር፣ በሀገር ቻይና እዳሪው ለማዳበሪያነት እና ለአሳማ ምግብነት ስለሚውል መጸዳጃ ቤት ገብተው የመጸዳዳት ፍላጎት አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ተግዳሮት የነበረ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ግን ከመጸዳጃ ቤት የሚወጣውን ፍሳሽ በባዮ ጋዝ አማካኝነት ለኃይል ምንጭ እና ለማዳበሪያነት እንዲያገለግል ተደርጎ ችግሩ ተፈትቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ዢ የመጸዳጃ አብዮትን ከመጀመራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ባለሙያዎች እንደ ተቅማጥ እና ወባ ያሉ ጥገኛ ተውሳኮችን እና ሌሎች በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ስርጭት ለመግታት በታዳጊ ሀገሮች የመጸዳጃ ቤት አብዮት እንዲካሄድ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

በቻይና የመጸዳጃ ቤት አብዮት ተግባራዊ በሆነ ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በከተሞች ውስጥ 68 ሺህ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል፤ ከ10 ሚሊዮን በላይ የገጠር መጸዳጃ ቤቶች ታድሰው ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

በ2009 ብቻ መጸዳጃ ቤቶችን ለማሻሻል 1 ቢሊዮን ዶላር በማዕከላዊ መንግሥት ወጪ ተደርጓል፤ ይህ ገንዘብ ግዛቶች ለዚህ ተግባር ያወጡትን ወጪ አይጨምርም። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የራሳቸውን ሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች እንዲከፍቱ ማበረታቻዎች ተሰጥቷቸዋል። በዚህም መሰረት የሀገሪቱ ብሔራዊ ቱሪዝም ፈንድ ከ2015 እስከ 2017 ለመርሐ ግብሩ 1.64 ቢሊዮን ዩዋን ወይም 232 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዋጥቷል።

                                      

እንደ ዓለም ባንክ ጥናት በቻይና የመጸዳጃ አብዮት ከታወጀ በኋላ መሰረታዊ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር እ.አ.አ በ2000 ከነበረበት 56.3 በመቶ በ2017 ወደ 84.8 በመቶ አድጓል፡፡ 85 በመቶ የሚሆኑት የገጠር ነዋሪዎች መሰረታዊ የመጸዳጃ ቤት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በቻይና የመጸዳጃ ቤቶች አገልግሎት ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም የተለመደ ሆኗል፡፡ ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው የሚገኘውን የሕዝብ መጸዳጃ ቤት እንዲለዩ እና የመጸዳጃ ቤቶቹን ደረጃ አውቀው እንዲመርጧቸው የሚያስችል መተግበሪያ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ተጠቃሚዎቹ እንደ የመጸዳጃ ወረቀት እና የሕፃናት ማቆያ መኖራቸውን፣ ክፍት ቦታዎች መኖራቸውን እና የክፍያ ሁኔታዎችን በመለየት ከፍላጎታቸው ጋር የሚስማማውን ለመምረጥ መተግበሪያውን ይጠቀማሉ። መተግበሪያው አየር ሁኔታን እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የሽታ ሁኔታ በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ በማመንጨት በአካባቢው ያሉ ኦፕሬተሮችን ያግዛል፡፡

መተግበሪያው እነዚህን መረጃዎች መስጠት ብቻ ሳይሆን መሻሻል ስለሚገባቸው ነገሮችም የተተነተነ ዳታ ያቀርባል፤ ለምሳሌ የሴቶች መጸዳጃ ቤቶች ከወንዶች ቢያንስ 50 በመቶ ሊበልጡ እንደሚገባ ከመተግበሪያው የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ የሴቶች መጸዳጃ ቤቶች በተለየ ሁኔታ እንዲገነቡ በመርሐ ግብሩ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል።

በአሁኑ ጊዜ በቱሪስት መዳረሻዎች እና በመጓጓዣ ጣቢያዎች ንጽህናቸውን እና ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች፣ አንዳንዴም በጣም ቅንጡ የሚባሉትን መጸዳጃ ቤቶች ማየት የተለመደ ሆኗል። የመጸዳጃ ቤት ወረቀቶችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ስርቆት ለመከላከል ፊትን ማንበብ የሚችሉ ማሽኖች፣ ስማርት ቴሌቪኖች፣ ማቀዝቀዣዎች እና ሌሎች ዘና የሚያደርጉ ቁሳቁሶች የተገጠሙላቸው መጸዳጃ ቤቶች ማየት ብርቅ አይደለም።

መጸዳጃ ቤቶቹ የውጪ ሀገር ጎብኚዎችን የተለየ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉም እንደ ነፃ ዋይፋይ፣ ኤቲኤም እንዲሁም የስልክ ባትሪ መሙያ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

                                   

ባለፈው ዓመት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በቀጣይ አሥርተ ዓመት መገባደጃ ላይ ሁሉንም የገጠር መጸዳጃ ቤቶችን ከፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ጋር የማያያዝ ሥራዎች ይሠራሉ።

ለመርሐ ግብሩ መሳካት መገናኛ ብዙኃን ትልቁን ድርሻ ወስደው ሠርተዋል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሚዲያዎች በመጸዳጃ ቤቶች ማሻሻል ሂደቱ ላይ የታዩ ጉድለቶችን ነቅሰው እንዲያሳዩ በተሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ተልዕኮውን በትክክል ተወጥተዋል፡፡

መጸዳጃ ቤቶችን ማሻሻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ጠቀሜታዎች መካከል ጤናማ ህብረተሰብን መፍጠር ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጽዱ አካባቢን መፍጠር የሀገርን ምስል ለማሻሻል የራሱን ድርሻ አለው፡፡

የዓለም መጸዳጃ ቤት ድርጅት መሥራች የሆኑት ጃክ ሲም፣ "መጸዳጃ ቤቶች ሰዎችን ከበሽታ ስለሚጠብቁ ሰዎች በቀላሉ እንዳይታመሙና አዘውትረው ወደ ሥራ እንዲሄዱ ያስችላቸዋል" ይላሉ፤ አክለውም፣ "ይህም ለሕክምና የሚውለውን ወጪ ስለሚቀንስ ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ጠቃሚ ነው" በማለት የመጸዳጃ ቤትችን መዘመን አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡   

ኢትዮጵያ “ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ቃል የመጸዳጃ ቤቶችን ግንባታ መርሐ-ግብር ይፋ አድርጋለች፡፡ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት ክብርን ጠብቆ የመፀዳዳት ባህልን ለማዳበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ የሆነውን የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄ በርካቶች በመቀላቀል ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል። በዚህ ንቅናቄ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ዜጎች አቅማቸው የፈቀደውን ገንዘብ በመደገፍ ለዓላማው መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የተጀመረው ንቅናቄ በቀጣይ ሀገር አቀፍ ሆኖ ጽዱ እና ጤናማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል፡፡

በለሚ ታደሰ

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top