ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ለማካተት የሚረዳ ጥናት ተደረገ

3 Days Ago
ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ለማካተት የሚረዳ ጥናት ተደረገ
ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ በትምህርት ሥርዓት እና በሙያ ተቋማት በማካተት ወደ ስልጠና ለማስገባት የሚረዳ ጥናት መደረጉን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
 
የኢንስቲትዩቱ የጥናት ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ የመገንባት ኢንሼቲቭ እንዲቀላጠፍ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ላቅ ያለ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
 
በጥናቱ በተለይ እየተተዉ እና እየተረሱ በመጥፋት ላይ የሚገኙ ሀገራዊ ዕውቀቶችን እና ተሰጥዖዎችን የመለየት ብሎም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመሰነድ ስራ እንደተሰራም ጠቁመዋል፡፡
 
የመንግስት የትኩረት ነጥቦች በሆኑት በግብርና፣ በማዕድን፣ በአምራች እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ለስልጠና እና ለቴክኖሎጂ አመቺ የሚሆኑት ላይ ትኩረት መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
 
ጥናቱ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል በመንቀሳቀስ የተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም 2ሺህ 500 ለቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ምቹ የሚሆኑ የሀገር በቀል ዕውቀቶች መገኘታቸውን እና በሳይንሳዊ መንገድ መሰነዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
 
የትምህርት ሥርዓቱ አውዳዊ እና ሀገራዊ ዕውቀትን ያላካተተ መሆኑ፤ የሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዲረሱ እና ቸል እንዲባሉ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
ለዘርፉ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ሰነድ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ እንዲሁም ለሌሎችም በዘርፉ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች መነሻ መሆን የሚችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
በቀጣይ የተገኙትን የጥናት መዳረሻዎች በትምህርት ሥርዓቱ ለማካተት ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top