የደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ይፋ ሆነ

22 Days Ago
የደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ይፋ ሆነ
በደቡብ አፍሪካ ትናንት የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ይፋ ሆኗል።
 
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ከ14 የምርጫ ክልሎች የሰበሰበውን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚሁ መሰረት ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ 43 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሲመራ ዲሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ደግሞ በ26 በመቶ ድምጽ ይከተላል።
 
በጁሊየስ ማሌማ የሚመራው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) እና በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የተመሰረተው “ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ” ፓርቲ (ኤምኬ ፓርቲ) በተመሳሳይ 8 በመቶ ገደማ ድምጽ ማግኘታቸው ተጠቁሟል።
 
የምርጫው የመጨረሻ ውጤት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
 
የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ከ30 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ ያለውን አብላጫ መቀመጫ ሊያጣ እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን ይህም ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግስት የመመስረት ግዴታ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል።
 
በደቡብ አፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋው ሙስና፣ የወንጀሎች መበራከት እና ስራ አጥነት ገዢው ፓርቲ ድጋፉን እንዲቀንስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱ ቢቢሲ ዘግቧል።
 
አንድ ፓርቲ በደቡብ አፍሪካ የምርጫ ስርዓት በፓርላማው አብላጫውን ድርሻ ለመያዝ ከ400 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ 201ዱን ማሸነፍ ይኖርበታል።
 
ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ እ.እ.አ በ1994 የአፓርታይድ ስርዓት ካከተመ በኋላ የተካሄዱ አምስት ምርጫዎችን በሙሉ ያሸነፈ ሲሆን የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ በአምስቱም ምርጫዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
 
ኤንሲ እ.አ.አ በ2019 በተካሄደው ምርጫ 57 ነጥብ 5 በመቶ ድምጽ ያገኘ ሲሆን ይህም ከቀደሙት ምርጫዎች ዝቅተኛ ድምጽ ያገኘበት መሆኑ ተመላክቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top