ሕጉ ምን ይላል - ውለታና ስጦታ

22 Days Ago
ሕጉ ምን ይላል - ውለታና ስጦታ

‘‘…ውለታስ ይሄው ነው ወይ?

ብድርስ ይሄው ነው ወይ?

ወረታስ ይሄው ነው ወይ?

ሰው አልወጣልኝም እኔስ አወይ አወይ!! ’’

ይህ የኬኔዲ መንገሻ ዘፈን አዝማች የዛሬውን ውለታ እና ስጦታን በተመለከተ ሕጉ ምን እንደሚል የምናይበት ፅሑፍ መግቢያ አድርገነዋል።

እማሆይ ወለተገብርኤል የዚህችን ዓለም ነገር በቃኝ ብለው ከመመንኮሳቸው በፊት ከሟች ባለቤታቸው ጋር ከነበራቸው የእርሻ መሬት ላይ ድርሻቸው የሆነው 1.65 ሄክታር ይደርሳቸዋል። ሆኖም ‘የእንጀራ ልጄ ባል’ ነው ያሉት ግለሰብ  መሬታቸውን በጉልበት ይዞ መጠቀም ጀመረ።

ይሄኔ ነበር አቶ ደረጀ እማሆይ ረዳት ማጣታቸውን አይቶ የቀረባቸው። ይዞታቸውንም ከግለሰቡ ተከላክሎ ረዳት አለኝታ ሆናቸው። ወደ አንድ ቤተክርስቲያን ወስዷቸው በእማሆይ አባባል ‘‘አብረን እንበላለን ልጄ ነው ብለሽ ፈርሚ’’ ብሎ የሆነ ሰነድ ላይ አስፈረማቸው።ይህ የሆነው በ1998 ዓ.ም የመጋቢት 23 ቀን ነበር።

ከዚያም አቶ ደረጀ መሬቱን እያረሰ እማሆይንም እየረዳቸው ቆይቶ። ከአንድ ዓመት በኋላ ምን እንደነካው እንጃ….. እማሆይ እንደሚሉት ‘‘አቅመ ደካማ መሆናቸውን አይቶ’’ እርዳታውን ያቋርጣል። እማሆይም እድሜያቸው የገፋ አቅመ ደካማ በመሆናቸው የሚረዳቸው አጥተው ተራቡ።ሌላ አማራጭ ሲያጡም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ተጠለሉ። ለውለታቸው ለሰጡት መሬት ቀለብ እንኳን ተነፈጉ። እማሆይ ነገሩን ለፈጣሪ ብቻ ሰጥተው አልተውትም።

በምድራዊው ዳኛ ዘንድ ከሰሱ። የእማሆይ ክስ የቀረበው በአካባቢያቸው በቀድሞው የደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አቤሼጌ ወረዳ ፍርድ ቤት ነበር። ክሱ ‘‘አቶ ደረጀ የማላውቀው ወረቀት ላይ አስፈርሞኝ የእርሻ መሬቴን ነጥቆኛል በመሆኑም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ያቋረጠብኝን በመሬቴ ላይ ያመረተውን ምርት ድርሻዬን ይስጠኝ መሬቴንም ይመልስልኝ’’ የሚል ነበር።

ተከሳሽ አቶ ደረጀም ለክሱ በሰጠው መልስ "እማሆይ በሕጋዊ የስጦታ ውል በ1998 ዓ.ም የመጋቢት ጊዮርጊስ ዕለት መሬታቸውን በስጦታ ሰጥተውኛልና ሊጠይቁኝ አይችሉም። መሬቱም በስሜ ዞሯል" ሲል ተከራከረ። ያን ጊዜ ያስፈረማቸውን የስጦታ ውልም አቀረበ።

የአቤሼጌ ወረዳ ፍርድ ቤትም በሰጠው ውሳኔ ‘‘ስጦታው ሕጋዊ ነው። እማሆይ ወደውና ፈቅደው ለአቶ ደረጀ መሬታቸውን መስጠታቸው እንጂ የስጦታ ውሉን በማታለል ያስፈረማቸው መሆኑ ስላልተረጋገጠ ደረጀ መሬቱን ሊለቅ አይገባም’’ ብሎ የእማሆይን ክስ ውድቅ አድርጎ ወሰነባቸው።

እማሆይ እጅ አልሰጡም። ለጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቁና ከባለጋራቸው ጋር ተከራክሩ። ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ‘‘የስጦታ ውሉ አልተመዘገበም። ቀበሌ በፃፈው ትዕዛዝ (ቀላጤ) የሰው መሬት ማስተላለፍ አይቻልም።  አቶ ደረጀ አለኝ የሚለው የስጦታ ውል በተንኮል ስለተደረገ ፈርሶ መሬቱን መልቀቅ አለበት።መሬቱን ለብቻው የተጠቀመበትንም ባካባቢው ባህል መሰረት ኪራዩን ይክፈል’’ በማለት የወረዳ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሽሮ ለእማሆይ ወሰነ።

አቶ ደረጀም በተራው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቀ። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አሟግቶ ‘‘የስጦታ ውሉ እንከን አልባ በመሆኑና አቶ ደረጀ መሬቱን አለስልሶ በስሙ አዛውሮ እየተጠቀመበት ስለሚገኝ የስጦታ ውል ግዴታውን አልተወጣም የሚል ክስም ስላልቀረበበት መሬቱን ሊለቅ አይገባም ’’ ብሎ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሻረና የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፀናው።

እማሆይ አሁንም ሙግቱን ቀጠሉበት። ‘የሕግ ስህተት ተፈፅሟል’ ብለው ለክልሉ ሰበር ሰሚ ያቀረቡት አቤቱታ ስላልተሳካ የመጨረሻው የዳኝነት ስልጣን ወዳለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ‘‘በስጦታ ውል አስታከው የስር ፍርድ ቤቶች መሬቴን በማስነጠቃቸው የሕግ ስህተት ስለፈፀሙ ይታረምልኝ’’ አሉ።

የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ‘‘እማሆይ መሬታቸውን በስጦታ ቢሰጡም ተቀባዩ እንዳይጦራቸው ብለው መሬታቸውን ለቀቁለት ተብሎ አይገመትም።ሕጉ በውል ላይ በግልፅ ባይሰፍርም ስጦታ ሰጪው በድህነት ላይ ሲወድቅ ስጦታ ተቀባዩ የመጦር ግዴታ እንዳለበት ደንግጓል።

አቶ ደረጀ ግን መሬቱን ይዘው እየተጠቀሙበት እንኳንስ እማሆይን መጦር ቀርቶ በውለታ ቢስነት ሀብቱን በስማቸው ማዞራቸውን ከክርክሩ የምንረዳው ነው። እማሆይ  ደግሞ አለመጦራቸውን ካረጋገጡ ይዞታቸውን ማስመለስና ስጦታው እንዲሻር የመጠየቅ መብታቸውን ሊነፈጉ አይገባም። ከይዞታቸው ላይ ያለመፈናቀል ሕገ መንግስታዊ መብትም አላቸው።" ብሎ ለውሳኔው መነሻ ምክንያቱን አሰፈረ።

የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀጠል አድርጎም "የደቡብ ክልል ሀዋሳ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ  ችሎቱ ‘‘አቶ ደረጀ በስጦታ ያገኘውን መሬት ሊለቅ አይገባም’’ በሚል የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽረው የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ማፅናታቸው ሊታረም የሚገባ በመሆኑ ሽሬዋለሁ’’ ብሎ ወሰነ።

‘’የእማሆይ መሬት እንዲመለስ እና አቶ ደረጀ ለብቻው መሬቱን አርሶ የተጠቀመበትንም በአካባቢው ባህል መሰረት የመሬት ኪራይ እንዲከፍላቸው" በሚል ተሰጥቶ የነበረውን የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በማፅናት አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ሰጥቷል።እማሆይም ተስፋ ሳይቆርጡ እስከመጨረሻው ተከራክረው መሬታቸውን አስመልሰዋል።

ስናጠቃልለው ስጦታ የተቀበለ ሁሉ ሰጪ ሲቸገር የመርዳት የህሊና ብቻ ሳይሆን የሕግ ግዴታም አለበት። ውለታ ያለባችሁም ውለታችሁን አትርሱ!! ለማንኛውም ‘‘ውለታስ ይሄው ነው ወይ?’’ በሚለው የኬኔዲ መንገሻ ሙዚቃ ውለታ ተበልቶብን ከማንጎራጎርም ሆነ፣ ውለታ ቢስ ሆነን ‘ሰው አልወጣልኝም’ ከመባል ይሰውረን። በምትኩ ‘‘ባለውለታዬ’’ የሚለውን የተፈራ ነጋሽን ሙዚቃ እያንጎራጎርን ውለታ የምንመልስ ያድርገን።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top