ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ይበልጥ ለማጎልበት ተተኪ ዲፕሎማቶች ላይ እየሰራች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

6 Days Ago
ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ይበልጥ ለማጎልበት ተተኪ ዲፕሎማቶች ላይ እየሰራች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ይበልጥ ለማጠናከር እና ለማሳደግ ተተኪ ዲፕሎማቶች ላይ እየሰራች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ገለፁ፡፡

ኢትዮጵያ የረጅም ግዜ ታሪክ፣ ባህል፣ ስልጣኔ እና ጥንታዊ ህዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ በወቅቱ ከነበሩ ሀገራት እና ህዝቦች ጋር ግንኙነት ነበራት ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህም ጥንታዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ካላቸው ሀገራት አንዷ እንድትሆን ማድረጉን ይገልፃሉ፡፡

የዓድዋ ድልን ተከትሎ ሀገራችን ያገኘችው እውቅና ሌሎች ሀገራት ከእርሷ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት የመመስረት ፍላጎትን ያመጣ እንደነበርም ነው የገለፁት፡፡

በ1900 ዓ.ም የተቋቋመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ቅርፅ አስይዞታል የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ ከዚያ ወቅት ጀምሮ የንግድ እና የወታደራዊ ቅርፅን የተላበሱ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች መዘውተራቸውንም ያነሳሉ፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት፣ የዓለም የፖስታ ድርጅት፣ የዓለም የቴሌ ኮሙዩኒኬሽን መቋቋም ዲፕሎማሲው አንድ እርምጃ ከፍ እንዲል ያስቻለው ስለመሆኑም ነው የገለፁት ፡፡

ኢትዮጵያ ይህን የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ልምዷን እና ስኬቷን ለማስቀጠል ብቁ ዲፕሎማቶችን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅባት አምባሳደሩ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በዘርፉ ተግዳሮት የሆነውን የአቅም ውስንነት ለመፍታት በቀጣይ ብዙ ስራዎችን ማከናወን እንደሚያፈልግም ነው የገለፁት፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመስኩ ተተኪ ለማፍራት መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ስርዓት በመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ብቁ የሆኑ ዲፕሎማቶችን ለማፍራት የአቅም ግንባታ፣ የአቅም መፈተኛ እንዲሁም የተለያዩ አጋዥ ስልጠናዎች ይሰጣሉም ነው ያሉት፡፡

አምባሳደር ነብዩ ዲፕሎማሲ ከሁለትዮሽ ተጠቃሚነቱ ባሻገር የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ ላቅ ያለ ሚና ያለው በመሆኑ ለተለያዩ ዘርፎች ማጎልበቻ እና ማሳደጊያ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በአፎሚያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top