የፍቺና የተለያይቶ መኖር ‘ፍቺ’

8 Days Ago
የፍቺና የተለያይቶ መኖር ‘ፍቺ’

ከፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተለያይቶ በመኖር ጋብቻ በሁኔታ እንደሚፈርስ የወሰነበት ክርክር ምን ነበር?

የፌዴሬሽን ምክር ቤትስ ይህን ውሳኔ መሰረት ያደረገውን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን ይቃረናል ሲል የሕግ ትርጉም የሰጠበት ክርክርስ ምን ይመስላል?

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለረጅም ጊዜ መለያየት ጋብቻን ያፈርሳል የሚያስብል አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የሰጠበት ክርክርን ተንተርሰን ጉዳዩን እንዲህ አቅርበነዋል።

አቶ ይልማ ነፍሳቸውን ይማርና በተለያየ ጊዜ ሁለት ሚስቶችን አገቡ። ከወ/ሮ ሳራ ጋር በ1966ዓ.ም፤ ከወ/ሮ ሸዋዬ ጋር ደግሞ በ1987 ዓ.ም ተጋቡ። አቶ ይልማ በ1989 ዓ.ም ከዚህ ዓለማ በሞት ተለዩ።

ይሄኔ ወ/ሮ ሳራ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ1995 ዓ.ም ‘‘የሟች የአቶ ይልማ ሚስትነቴ ይወሰንልኝ’’ ብለው አመለከቱ። ፍርድ ቤቱም ‘‘ወ/ሮ ሳራ እስከ አቶ ይልማ እለተ ሞት ድረስ የሟች የአቶ ይልማ ሚስት ነበሩ’’ ሲል ወሰነ ፡፡

ወ/ሮ ሸዋዬ ውሳኔውን እንደሰሙ ‘‘ሟች እስከ ሞቱበት ቀን የእኔ ባል ብቻ ናቸው። ከወ/ሮ ሳራ ጋር የነበራቸው ጋብቻ በ1977 ዓ.ም ፈርሷል። ወ/ሮ ሳራም ሌላ ባል አግብተው ሁለት ልጆች ወልደዋል፡፡ስለዚህ የሟች ሚስት ናቸው ሊባሉ አይገባም’’ ሲሉ ወ/ሮ ሳራ የሟች ሚስት ነበሩ የሚለው ውሳኔ እንዲሻር ለፍርድ ቤቱ አመለከቱ፡፡

ወ/ሮ ሳራም በበኩላቸው ‘‘በሟችና በኔ መሀከል የነበረው ጋብቻ በሕጉ በተቀመጡት የጋብቻ ማፍረሻዎች (በፍቺ፣ በአንደኛው ተጋቢ መሞት ወይም መጥፋት፣ በሕግ የተከለከለ ጋብቻ በመሆኑ በተሰጠ የፍርድ ቤት ውሳኔ) መፍረሱ ስላልተረጋገጠ ከሌላ ሰው ሁለት መውለዴና ተለያይተን ለየብቻ መኖራችን የነበረንን ጋብቻ አያፈርሰውም። ስለዚህ የሚስትነቴ ውሳኔ ሊሻር አይገባውም’’ ሲሉ መልስ ሰጡ፡፡

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ‘‘ወ/ሮ ሳራና አቶ ይልማ ተለያይተው ቢኖሩም፤ ወ/ሮ ሳራ ሁለት ልጆች ከሌላ ሰው ቢወልዱም፤ ሟች ወ/ሮ ሸዋዬን ቢያገቡም ወ/ሮ ሸዋዬ እንደሚሉት በሟችና በወ/ሮ ሳራ በ1966 ዓ.ም የተፈፀመው ጋብቻ መፍረሱን የሚያሳይ ማስረጃ ስላላቀረቡ የወ/ሮ ሳራ ሚስነትነትን አረጋግጬ የሰጠሁትን ውሳኔ የምሽርበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ’’ ሲል ወሰነ።

ወ/ሮ ሸዋዬ ውሳኔው ስላልተዋጠላቸው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም አልተሳካላቸውም። ተስፋ ሳይቆርጡ ቀጠሉና ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘‘የሕግ ስህተት በበታች ፍርድ ቤቶች ተፈጽሟልና ይታረምልኝ። ለወ/ሮ ሳራ የተሰጠው የሚስትነት ውሳኔ ይሻርልኝ’’ ሲሉ የሰበር አቤቱታ አቀረቡ ፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት መዝገብን አስቀርቦ ባደረገው ምርመራ ወ/ሮ ሳራ ለስር ፍርድ ቤት በሰጡት ቃል ‘‘በ1985ዓ.ም ከአቶ ይልማ ጋር ተጣልተው አዲስ አበባ መምጣታቸውንና ነገር ግን ከሟች ጋር የነበራቸው ጋብቻ በፍቺ አለመፍረሱን፣ ሟችም ወ/ሮ ሸዋዬን አግብተው ወደ አጋሮ መሄዳቸውን እንደሰሙ’’ መግለፃቸውን ተረዳ።

ወ/ሮ ሸዋዬም በስር ፍርድ ቤት ‘‘በወ/ሮ ሳራና በአቶ ይልማ መሀል የነበረው ጋብቻ በፍቺ መፍረሱን ያውቁ ነበር?’’ ተብለው ሲጠየቁ፤ ‘‘ሟች ከወ/ሮ ሳራ ጋር ተጋብተው እንደነበርም ስለማላውቅ ፍቺውንም አላውቅም ነበር።’’ ብለው መልሰው እንደነበርም ከስር ፍርድ ቤት መዝገብ አረጋገጠ።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 20938 ሚያዚያ 1 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ እንዲህ አለ፡፡ ‘‘በወ/ሮ ሳራና በአቶ ይልማ መሀል የነበረው ጋብቻ በሕጉ በተቀመጡ የጋብቻ ማፍረሻዎች ባይፈርስም በስር ፍርድ ቤት ወ/ሮ ሳራ የሰጡት ቃል መፍረሱን የሚያሳይ ነው። ወ/ሮ ሳራና አቶ ይልማ በጋብቻው መቀጠል ባለመቻላቸው ተጣልተውና ተለያይተው በየፊናቸው የየራሳቸውን ኑሮ ሲኖሩም ነበር።

በመሀከላቸውም ለጋብቻው መፍረስ የሚያበቁ ምክንያቶች መኖራቸውንና አቶ ይልማም ወ/ሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ወ/ሮ ሳራ ያውቁት ነበር። ሆኖም ሁለቱም የየራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ስለነበር ወ/ሮ ሳራ አቶ ይልማ ወ/ሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ቢያውቁም ሟች በህይወት እያሉ ጋብቻውን ‘በጋብቻዬ ላይ የተፈፀመ ሕገወጥ ጋብቻ ነው’ ብለው አልተቃወሙትም።

‘‘… ሰለዚህ የስር ፍርድ ቤቶች ይህን ባረጋገጠበት ሁኔታ ‘ወ/ሮ ሳራ ሟች እስከሞቱበት እለት ሚስት ነበሩ’ ብለው መወሰናቸው ትክክለኛውን የሕግ አተረጓጎም የተከተለ አይደለም። ፍቺ መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡ ብቻ አንድን ጋብቻ የፀናና ውጤት የሚያስከትል ነው ሊያስብለውም አይችልም።

ባለመግባባት ተለያይተው ፍቺ ለመፈፀም የሚያስችል ምክንያት የነበራቸው ተጋቢዎች የየራሳቸውን ኑሮ በየበኩላቸው ጀምረው ከኖሩ በኋላ ባል ወይም ሚስት ናቸው ሊባሉ አይችሉም።’’ የሚለውን የሕግ ትርጉም በመስጠት ለወ/ሮ ሳራ ሚስትነት እውቅና የሰጠውን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮታል።

ስናጠቃልለው በጋብቻ ውስጥ ባልና ሚስት ተስማምተው ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው መኖር ይችላሉ። ሆኖም ከጋብቻ የሚጠበቁት የባልና የሚስት ግዴታዎች መተማመኑ፣ መከባበሩ፣ መተጋገዝና ቤተሰብን በጋራ መምራቱ በርቀትም ቢሆን መቋረጥ የለባቸውም። ተለያይቶ በመኖሩ ላይ አንደኛቸው ካልተስማሙበትና የየራሳቸውን ኑሮ በግላቸው ከቀጠሉ ግን ጋብቻው በሕግ ባይፈርስም በተግባር ግን አፍርሰውታልና ጋብቻ አለኝ ማለት አይችሉም።

ጋብቻ በሁኔታ ይፈርሳል የሚለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠበት መዝገብ ከላይ ያነሳነው ነበር።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ይህ የሰበር ትርጓሜ መሰረት ያደረገው የጋብቻ በፍቺ መፍረስ በቤተሰብ ሕጉ ከተቀመጡት ጋብቻን የሚያፈርሱ ምክንያቶችና ፍርድ ቤት የጋብቻን መፍረስ እና ውጤቶቹን የንብረት ክፍፍል እና የልጆች አስተዳደግን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የመወሰን ሥልጣኑን በመጋፋት ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሕግ አውጭውን ሥልጣን በመጋራት ተጨማሪ በሕግ ከተቀመጠው ውጭ የጋብቻ ማፍረሻ መንገድ የወሰነበት በመሆኑ የሰበር ውሳኔውና ይህን መሰረት በማድረግ የተሰጠው ውሳኔ የቤተሰብ ሕጉን ድንጋጌ እና ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡት የሥልጣን ክፍፍሎችን በመቃረን በሕግ አውጭው ያልተደነገገ የጋብቻ ማፍረሻ ሕግ በአስገዳጅ ውሳኔው ያወጣበት በመሆኑ ሕገ መንግስቱን ይቃረናል ሲል ሽሮታል።

ለረጅም ጊዜ መለያየት ፍቺን ሊያስከትል ይገባል ወይስ አይገባም። ሀሳባችሁን ሰንዝሩና እንወያይበት።

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top