የዲፕሎማሲ ማዕከሏ - ጄኔቫ

23 Days Ago
የዲፕሎማሲ ማዕከሏ - ጄኔቫ

በውብ ገጽታዋ የምትታወቀው የስዊዘርላንዷ ጄኔቭ ከተማ ስመጥር ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መቀመጫ ናት። ከዙሪክ በመቀጠል በሀገሪቱ ሁለተኛዋ ሰፊ የህዝብ ብዛት ያላት ከተማዋ፣ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በስፋት ይነገርባታል። 

የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮኖች መቀመጫ በመሆን “የሰላም ዋና ከተማ” የሚል መጠሪያ ያገኘችው ጄኔቭ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ከ40 በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በውስጧ ይዛለች። 

ከእነዚህም ውስጥ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት፣ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ይጠቀሳሉ። 

በእጅ ሰዓት ስራ ግዙፍ ስም ያላት ከተማዋ፣ የበርካታ ስመጥር የእጅ እና የግድግዳ ሰዓት አምራች ኩባንያዎች መገኛ ናት። 

በታሪክ እና በባህል የበለፀገችው ከተማዋ፣ ትናንቷን የሚዘክሩ በርካታ አሻራዎቿን ጠብቃ በመያዝ ታሪክን ከስልጣኔ ጋር አስማምታለች። 

ከተማዋ ለታሪክ እና ለሥነ-ሕንፃ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የግድ መጎብኘት አለባትም ተብሎላታል። 

ለቱሪስቶች አስተማማኝ ደህንነት ካላቸው የዓለም ከተሞች ውስጥ አንዷ የሆነችው ጄኔቭ፣ ንጽሕና መለያዋ ነው። ጥብቅ የንጽሕና አጠባበቅ ሕግ እና መመሪያ ያላት ጄኔቭ፣ በሀገሬው ሰውም በእንግዳውም ታይታ የማትጠገብ ይባልላታል። 

የከተማዋን ደህንነት እና ንፅህና ለመጠበቅ የወጡ በርካታ አስደናቂ ሕጎችም አሏት፤ በከተማዋ ቆሻሻን በሕዝብ አደባባዮች መጣል ሕገወጥ ነው። 

ከተማዋ ለንፅህናን አስፈላጊነት አፅንዖት በመስጠት፣ ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች ቆሻሻን በአግባቡ እንዲያስወግዱ ታስገድዳለች። 

ጄኔቭ በአውሮፓ ውስጥ ካሉ የትላልቅ የውሃ ሐይቆች ባለቤቶችም አንዷ ናት፤ በከተማዋ የሚገኙ ጠባብና ጠመዝማዛ መንገዶች፣ ታሪካዊ ሕንፃዎች ውበት አላብሰዋታል። 

ከተማዋ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጥብቅ የሲጋራ ሕጎችን ተግባራዊ ታደርጋለች፤ በዚህም በህዝብ አደባባዮች እንዲሁም በምግብ ቤቶች እና በህዝብ ማመላለሻዎች ውስጥ ማጨስ የተከለከለ ነው። ይህ ሕግ ለሁሉም ሰው ጤናማ እና አስደሳች አካባቢን ለመፍጠር ያለመ ነው። 

ጄኔቭ የድምፅ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሕጎችም አሏት፤ ለአብነትም በመኖሪያ አካባቢዎች በተለይ በማታ የድምፅ መጠንን የሚገድቡ ልዩ መመሪያዎች ያሏት ከተማ ናት። እነዚህ ሕጎች ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች ሰላምና እና ጸጥታን ለማጎናጸፍ ያለሙ ናቸው። 

ከተማዋ እጅግ የዘመነ የህዝብ ትራንስፖርት ሥርዓት ያላት ከተማም ናት፤ የአውቶቡስ እና የከተማ ባቡር አገልግሎቷ በምቾቱ እና በቅልጥፍናው ምስጉን ነው። በሌላ በኩል በከተማዋ ብስክሌትን ዘላቂ የመጓጓዣ ዘዴ ለማደረግ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት አስፈላጊው መሠረተ ልማት ተዘርግቷል። 

ይህ ብቻም አይደለም፤ በጄኔቭ ባሉ ሆቴሎች የሚቆዩ ጎብኚዎች በቆይታቸው የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎትን በነጻ ለመጠቀም የሚያስችል "የጄኔቫ ትራንስፖርት ካርድ" የማግኘት መብት አላቸው። ይህ ካርድ በጄኔቭ ሐይቅ ላይ ያሉ አውቶቡሶችን፣ ባቡሮችን እና ጀልባዎችን ሳይቀር ለመጠቀም ያስችላል፤ ይህም ለቱሪስቶች ከተማዋን ለማሰስ ምቹ እና ወጪ ቆጣቢ አድርጎላቸዋል። 

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top