ህብረተሰቡ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት እንዲረባረብ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ

2 Days Ago
ህብረተሰቡ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት እንዲረባረብ  ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ
የሰውን እና የተፈጥሮን የተዛባ ግንኙነት ለማስታረቅ ህብረተሰቡ በስፋት ችግኞችን በመትከል፣ የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት እንዲረባረብ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በአማራ ክልል የዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በባሕር ዳር ተካሂዷል።
 
በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት በመዛባቱ ምክንያት የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እያስጨነቀ ያለ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል ብለዋል።
 
ይህን ችግር ለመቀልበስ ዋነኛው መንገድ ችግኞችን መትከልና የተፍጥሮ ሐብት ጥበቃን ማጠናከር መሆኑን በመጠቆም፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ችግኝ መትከል ያስፈልጋል ብለዋል።
 
ህብረተሰቡን በነቂስ በማሳተፍ የዚህን ዓመት ዕቅድ ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
 
"የምትተክል ሀገር፣ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብር እንደሚካሄድም ተገልጿል።
 
በክልሉ በመጀመሪያ ዙር የአረንጋዴ አሻራ መርሐ-ግብር 7.3 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የፅድቀት ምጣኔው 79 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷልም ተብሏል።
 
ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጋዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአማራ ክልልን የደን ሽፋን ከ14 ነጥብ 2 ወደ 16 ነጥብ 3 ከፍ እንዲል ማስቻሉም ተጠቁሟል።
 
በዚህ ዓመት የአረንጋዴ አሻራ መርሐ-ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገልፀዋል።
 
ከ201 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በችግኝ እንደሚሸፈንም ነው የጠቆሙት።
 
በዚህ ዓመት የችግኝ ተከላን በክላስተር ለማከናወን እና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማካሄድ እንደሚሰራም ተገልጿል።
 
በይሄነው ዋጋቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top