የተሸጠ ዕቃ ገንዘብ መልስልኝ ክርክር በሕግ ዓይን

3 Days Ago
የተሸጠ ዕቃ ገንዘብ መልስልኝ ክርክር በሕግ ዓይን

ሜሮን ከአንድ አስመጪ የአዳማ ቅርንጫፍ በ16,750.00 ብር ማቀዝቀዣ(ፍሪጅ) ገዛች። የአንድ ዓመት ዋስትና አለው። ከዛም ማቀዝቀዣውን ቤቷ ወስዳ ስትሞክረው አይሠራም። መልሳ ወደ ገዛችበት በመውሰድ ለሻጩ ስታሳውቅ ግድ የለም ይስተካከላል ተባለች። በዚህ ተስማምታ ተስተካክሏል ብላ ቤቷ የወሰደችው ማቀዝቀዣ ለሁለተኛ ጊዜ አልሠራም ይላል፡፡

አሁንም ድጋሚ ወደ ሻጩ ወሰደችው። አሁን ግን ‘‘ይህን አስሬ የሚበላሽ ዕቃ ሳመላልስ አልኖርም!’’ ብላ በሌላ አዲስ ፍሪጅ ይቀየርልኝ ስትል ጠየቀች። ይሄኔ ሻጩ ‘‘ብልሽቱን አስተካክለን ማቀዝቀዣው አሁን እየሠራ ስለሚገኝ ውሰጅ እንጂ አልቀይርም!’’ አለ። ቢባል ቢሠራ!! ወይ ፍንክች!!

ወ∕ሮ ሜሮን ከላይ ያነሳነውን የጉዳዩን መነሻ ጠቅሳ ‘‘ወይ አዲስ ማቀዝቀዣ ይተካልኝ ወይ ገንዘቤ ይመለስልኝ’’ ስትል ለአዳማ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቀረበች።

ተከሳሹ ሻጭም ለክሱ በሰጠው መልስ “በእርግጥ የተባለውን ማቀዝቀዣ ለከሳሽ ሽጫለሁ፤ ነገር ግን ለአንድ ዓመት የሰጠሁት የጥገና ዋስትና በመሆኑና ብልሽቱ ስለተጠገነ በሌላ የመቀየር ወይም ገንዘቡን የመመለስ ግዴታ የለብኝም፤ ስለዚህ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ“ አለ።

ፍርድ ቤቱም ማቀዝቀዣው መስራት አለመስራቱን ቦታው ላይ ተገኝቶ ተመለከተና

‘‘ ሻጭ በውል ግዴታው መሰረት የተበላሸውን ስለጠገነ ክሱን አልተቀበልኩትም’’ ሲል ወሰነ።

ወ∕ሮ ሜሮን  ይግባኝ ጠየቀች ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት።

ፍርድ ቤቱም ከኦሜዳድና ከሳልኔት ድርጅቶች ሁለት ባለሙያዎች ተመድበው ማቀዝቀዣው መሥራቱን እንዲያጣሩ አዘዘ። ሆኖም ሻጭ ሳልኔትን ብቻ አስመርምሮ በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ ከቅን ልቦና ውጭ ያደረገው ነው ብሎ ሌላ አዲስ ተመሳሳይ ሞዴል ማቀዝቀዣ ለይግባኝ ባይ እንዲተካላት ወይም ገንዘቡን ሻጭ እንዲመልስ ወሰነ።

አሁን ደግሞ የይግባኙ ተራ የሻጭ ሆነ።

ሻጭም በየደረጃው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎቱ ያቀረበው ይግባኝ አልተሳካም። በመጨረሻም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ አለ።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክርና የስር ፍርድ ቤትን መዝገብ መርምሮ…. ‘‘ ወ∕ሮ ሜሮን  የተበላሸውን ማቀዝቀዣ ለሻጭ አቅርባ ብልሽቱ መሠራቱ በባለሙያ ተረጋግጧል። በሽያጭ ውሉ ላይ ሻጭ ለአንድ ዓመት ብልሽት ካጋጠመ ለመጠገን በገባው ግዴታ መሰረት ማቀዝቀዣውን ጠግኗል።

የቀረበው ክስም ሻጭ የሸጠው ዕቃ ላይ ለተከሰተው ድብቅ ጉድለት ኃላፊነት አለበት በሚል የቀረበ ባለመሆኑ በሌላ አዲስ ማቀዝቀዣ የመተካት ወይም የተገዛበትን ገንዘብ የመመለስ ግዴታ የለበትም ’’ ብሎ ወሰነ። የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻርም የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፀናው።

ይህ ውሳኔም ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም የተሰጠ ሲሆን በቅጽ 17 የሰበር ውሳኔዎች ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ነገርን ነገር ያነሳዋልና ‘’ለመሆኑ ዕቃ ስትገዙ ምን ማድረግ አለባችሁ?’’ የሚለውን ነጥብ እንመልከት።

ዕቃውን ከመረከባችሁና ዋጋውን ከመክፈላችሁ በፊት ለመግዛት የተስማማችሁት አይነት፣ ብዛት፣ መጠንና ጥራት ያለው መሆኑን መመርመር የናንተ ግዴታ መሆኑን የፍትሐ ብሔር ሕጉ በቁጥር 2291 ላይ ጠቅሷል።

ምርመራው እንደ አካባቢው ልማድ ነው። ለምሳሌ አምፖል ስትገዛ ማቀፊያው ውስጥ ከተህ አብርተህ ትሞክራለህ። እንቁላል ስትገዛ ወደ ፀሀይ ብርሃን አዙረህ ታያለህ። ለሌላም ዕቃ እንደየ ዕቃው ባህሪ የተለመዱ ፍተሻዎች አሉ።

በዚህ ልማዳዊ ምርመራ ሊታወቅ ያልቻለ ጉድለት ካለና ዕቃውን ከተረከብክ በኋላ ከተገኘ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕጉ 2293 መሰረት ጉድለቱን እንዳወክ ‘ወዲያው በፍጥነት’ ለሻጭ ማሳወቅ አለብህ።

 

ጉድለት እንዳለበት እያወክ ከገዛህ ሻጭ ዋስትና ቢሰጥህም አይጠየቅም።

ጉድለቱ ግልፅ ሆኖ እየታየ በከባድ ቸልተኝነት ሳታዩት ከገዛችሁም አለቀላችሁ። በዚህ ቸልተኛነትህ ሻጭ ለጉድለቱ ኃላፊ የሚሆነውም በግልፅ ‘‘ዕቃዬ አንዳችም ጉድለት የለበትም!’’ ብሎ ማረጋገጫ ከሰጠህ ብቻ ነው።

ዋስትና ወይም ለተሸጠ ዕቃ የሻጭ ዋቢነት ነጋዴዎቻችን በማስታወቂያቸው ላይ የአንድ ዓመት የሁለት ዓመት ዋስትና እያሉ ለደንበኞች አስበው ያደረጉት ችሮታ እንደሚያስመስሉት አይደለም። በሕግ ያለ ወይም በውል የሚፈጠር የሻጭ ግዴታ ነው።

ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጠው ዋስትና በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2294 መሰረት ሻጭ የተወሰነ ጊዜ አስቀምጦ ለዕቃው የተወሰነ ሁኔታ ወይም መልካም አገልግሎት ዋቢ የመሆን ግዴታ የሚገባበት የውል ስምምነት ነው። በሽያጭ ውሉ ላይ ሻጩ የሕግ የዋቢነት ግዴታውንም ሊቀንስ ወይም ሊያስቀርም ይችላል። በመሆኑም ገዢዎች የውሉን ድንጋጌዎች በደምብ ማየት አለባቸው። ሻጭ ይህን አይነት ለሸጠው ዕቃ ለተወሰነ ጊዜ የዋስትና የውል ግዴታ ባይገባም የሸጠውን ዕቃ ያስረከበው እንደውሉ በትክክል ለመሆኑና ጉድለት እንደሌለበት ለገዢ መድን (አላፊ) እንደሆነ የፍትሀ ብሔር ሕጋችን 2287 ላይ ግዴታ ተጥሎበታል።

የምትገዛው ዕቃው የተሟላና ጉድለት የሌለበት መሆኑ የሚወሰነው ዕቃውን ከመረከብህ በፊት በነበረበት ሁኔታ ነው። በመሆኑም ዕቃውን ከመረከብህ በፊት እንደ ዕቃው ባህሪና ያካባቢው ልማድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ አለብህ።

በምርመራው መሠረት ዕቃው እንደ ውሉ የተሟላ ካልሆነና ጉድለት ካለበት ለሻጩ ባጭር ጊዜ ማሳወቅ አለብህ። ይህ አጭር ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ አልተገለፀም በሸማቾች ጥበቃ አዋጁ አንቀፅ 20(2) ላይ ግን ሸማቹ በ15 ቀናት ለሻጩ ጉድለቱን ማሳወቅ አንዳለበት ተደንግጓል።

ዕቃው ጉድለት ያለበት መሆኑን ለሻጭ አሳውቃችሁ በምትፈልጉት መልኩ ካልተስተካከለ ደግሞ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ክስ ማቅረብ አለብህ።

ሻጭ የሰጠህ የተወሰነ የዋስትና ጊዜ ካለ የአንድ አመቱ ክስ የማቅረቢያ ጊዜ የሚቆጠረው የዋስትናው ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ ነው። ይህ ጊዜ ካለፈ ግን መጠየቅ አትችልም። ሆኖም ያልከፈልከው የዕቃው ዋጋ ካለብህ ቀንሰህ ማስቀረት ወይም ለደረሰብህ ጉዳት መቃወሚያ ልታረገው ትችላለህ። 

ሻጭ ደግሞ ጉድለቱ ሲገለፅለት በፍትሀ ብሔር ሕጋችን 2301 መሰረት ለገዢ የሸጠው ነገር ላይ በተገኙት ጉድለቶች ፈንታ አዲስ መተካት ወይም በቂ በሆነ ጊዜ ጉድለቶቹን የማደስ መብት አለው።

ገዢ ደግሞ ጉድለቱን አሳውቆ በሚፈልገው መልኩ ከተስተካከለ እሰየሁ!! ካልሆነ ግን በተቀመጠው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ውሉ እንዲፈርስ ወይም በውሉ መሰረት እንዲፈፀም መክሰስ ይችላል።

በጉድለቱ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት ካለም ካሳ መጠየቅ መብት አለው።

የምንገዛውን ዕቃ ለምንፈልገው አገልግሎት የተሟላ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። የማናውቀውና ያልተስማማንበት ጉድለት ካለ ግን ሻጭ ዋስ ነው።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top