የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው በጀት ዓመት የ8.3 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታቅዷል - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

6 Mons Ago 980
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው በጀት ዓመት የ8.3 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታቅዷል - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

በ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚው የ8 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ መታቀዱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድን መገምገሙ ይታወቃል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች በዓመቱ የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚመዘገብ አመላካች ናቸው።

በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች የታየው አፈፃጸም የተቀመጠውን የኢኮኖሚ እድገት እውን ማድረግ  የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ በመኸር ወቅት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር 100 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተጀመሩ የበጋ መስኖ ስንዴና የሌማት ትሩፋት ስራዎችም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው ብለዋል።

ለአብነትም ከበጋ መስኖ ስንዴ ብቻ 117 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ ብቻ 106 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስረድተዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለፋብሪካዎች የግብዓትና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ ምርታማነት መጨመሩን አብራርተዋል።

በማዕድን ዘርፉ የወርቅና የሲሚንቶ ምርት መሻሻል ማሳየቱን ጠቅሰው ለአብነትም የሲሚንቶ ምርት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ከ1 ሚሊዮን ቶን በላይ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ከውጭ መሰረታዊ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግና የገበያ መሰረተ ልማትን በማስፋት አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን ወደ 23 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የአገልግሎት ዘርፉም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ዕድገት እያስመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ጥቅል ሀገራዊ ኢኮኖሚው የ8 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ መታቀዱንም አስረድተዋል።

የታቀደው የኢኮኖሚ ዕድገት አሁን ያለውን አቅምና ወደ ፊት መድረስ  የሚቻልበትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ እስከ በጀት ሰፊ ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ግቡን ለማሳካት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጅታል ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራርን ይበጥል አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሰረተ ልማቶችን ታሳቢ በማድረግ ድህነትን በሚፈለገው ልክ ለመቀነስ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሚቀጥለው በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የአሰራር ማሻሻያን አጠናክሮ መቀጠል፣ ምርትና  ምርታማነትን ማሳደግ፣ የገበያ መሰረተ ልማቶችን የማዘመን ስራ በስፋት ይተገበራሉ ነው ያሉት ሚኒስትሯ።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top