ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

2 Days Ago
ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
በሐረሪ ክልል ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው የሀገር አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
 
በዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የስነ ልቦና ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት፤ ተማሪዎች ጊዜና ጉልበታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ በማዋል ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ መሆን ይገባቸዋል።
 
በተለይም ተማሪዎች ፍርሃትና ጭንቀትን በማስወገድ እና በራስ መተማመንን በማዳበር ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
 
የክልሉ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው የሀገር አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
 
ተማሪዎች ኩረጃና ስርቆትን በመጠየፍ የራስ ስራ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው አቶ ኦርዲን በድሪ ምክር የለገሱት።
 
በተግዳሮት የማይሸነፍ፣ ለሀገር ሰላምና አብሮነት ቅድሚያ የሚሰጥ ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር የሚያስችል ሥራም በክልሉ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ብቁ፣ የነገ ሀገር ተረካቢና ለሀገር ጠቃሚ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
 
በሐረሪ ክልል በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከመንግስትና ከግል ትምህርት ቤቶች 2ሺህ 551 ተማሪዎች እንደሚፈተኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top