ሽንት በምንመገበው ምግብ፣ በምንወሰደው መድኃኒት እንዲሁም በምንጠጣው የውኃ መጠን ምክንያት ቀለሙ፣ ጠረኑ እንዲሁም ዓይነቱ ይቀያየራል።
ሽንት ሰውነታችን በፈሳሽ መልክ ቆሻሻን የሚያስወግድበት አንዱ መንገድ ሲሆን በዋናነት ውኃ፣ ጨው፣ ኤሌክትሮላይቶች እንደ ፖታሺየም እና ፎስፈረስ፣ ዩሪያ እና ዩሪክ አሲድ የሚባሉ ኬሚካሎች በውስጡ ይዞ ይገኛል።
እነዚህም ኩላሊት መርዛማ ንጥረ ነገሮችን እና ሌሎች መጥፎ ነገሮችን ከደም ውስጥ ሲያጣራ የሚከሰቱ ሲሆኑ፤ መድኃኒት፣ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች እና ሕመሞች የሚወገደው የሽንት ዓይነት ላይ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋሉ።
ጤናችን ያለበትን ሁኔታ የሚነግሩን የቀለም ዓይነቶች እንዳሉ ስንቶቻችን እናውቃለን?
ሽንት ፈዛዛ ቢጫ ወይንም ወርቃማ ቀለም ሲኖረው ሰውነት በቂ ውኃ አግኝቷል፤ ጤናማ ነው እንላለን።
ሽንት ምንም ዓይነት ቀለም ከሌለው (ውኃ ቀለም) ከሆነ ደግሞ ሰውነታችን በብዛት ውኃ እንዳገኘ እና እንዳበዛን ያመላክታል።
ከልክ በላይ ውኃ ማብዛት በሰውነታችን ወስጥ የኤሌክትሮላይት መዛባት ያስከትላል፤ በመሆኑም የምንወስደውን የውኃ መጠን በመቀነስ በቀን ውስጥ ከ6 እስከ 8 ብርጭቆ ውኃ እንድንጠጣ ይመከራል።
ቀላ ያለ ሮዝ ቀለም ለኩላሊት እና ለተለያዩ በሽታዎች መጋለጥን ሊያመላክት ይችላል።
አረንጓዴ ወይም ሰማያዊ የሽንት ቀለም በዘር ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች እና የሌሎች በሽታዎች ምልክት ሊሆን ይችላል።
ደማቅ ቢጫ ጤናማነትን የሚያሳይ ቢሆንም ይበልጥ ውኃ መጠጣት እንደሚያስፈልግ ግን ያመላክታል።
ቡናማ ቢጫ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት እንዲሁም የጉበት በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል።
እንደ ካሮት፣ ቀይ ስር እና የተለያየ ቀለም ያላቸው ምግቦች ሽንትን ወደ ቀይ ወይም ሮዝ ቀለም ይቀይሩታል። አንዳንድ መድኃኒቶች እንዲሁ የሽንት ቀለምን እና ጠረንን የመቀየር አቅም አላቸው።
ከነዚህ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የሽንት ቀለም ለውጦች በአጭር ቀናት ውስጥ ተመልሰው የሚስተካከሉ ናቸው።
ከዚህ ባለፈ የሰውነታችን ጤና ያለበትን ሁኔታ የሚያመላክቱ ከጤናማው ቀለም ለየት ያሉ ምልክቶች ሲኖሩ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።