የሴቶችና ህጻናትን የወደፊት እድልና ተስፋ ለማለምለም የወጠኑት ተግባር በፅንፍኛው ሃይሎች ሰይፍ ከመቀላት ያላስጣላቸው የገርጨጭ ሰማዕታት

1 Mon Ago 368
የሴቶችና ህጻናትን የወደፊት እድልና ተስፋ ለማለምለም የወጠኑት ተግባር በፅንፍኛው ሃይሎች ሰይፍ ከመቀላት ያላስጣላቸው የገርጨጭ ሰማዕታት

በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ ልዩ ስሙ ገርጨጭ የተባለው አካባቢ  ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሁንም በስፋት ካለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ይህ አስከፊ ድርጊት በተለይም የበርካታ የአካባቢው ሴቶችና ህጻናትን የወደፊት እድልና ተስፋ እያጨለመ ይገኛል፡፡

በክልሉ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራው አምረፍ ኸልዝ አፍሪካም ይህንን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት ስራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ ስር የሰደደ ነውና ችግሩን ከስሩ ለመንቀል ተሰሚ የአካባቢው ተወላጆችን በማሳተፍ ነው ተግባሩን እየከወነ ያለው፡፡

እናም የአገር ሽማግሌዎች፣ ቄሶች እና እናቶችን ያከተተ ቡድን በገርጨጭ ነዋሪዎች ተወክሎ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስወገድ ከአምረፍ ጋር ስራ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

ተወካዮቹም ከድርጁቱ በሚደረግላቸው ስልጠና እና ድጋፍ ህብረተሰቡን ያስተማራሉ፤ ያስተባብራሉ፡፡

ከሰሞኑም የድርጅቱን ተግባር እና እቅድ ለመግመገም በባህርዳር በተዘጋጀው መድረክ እንዲሳተፉ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች መምሪያ በኩል ለገርጨጭ አምረፍ ተወካዮች ጥሪ ይደረግላቸዋል፡፡

የማህበረሰቡ ተወካዮችም በተቋሙ የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ ወደ ባህርዳር ማቅናታቸውን የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል፡፡

የገርጨጭ የአምረፍ ተወካዮች በአካበቢያቸው የተንሰራፋውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እስከወዲያኛው ለማስወገድ መክረው ሲመለሱም ነው በታጠቁት ፅንፈኛ ሃይሎች ስር የወደቁት ሲሉም ይገልፃሉ አቶ አሰፋ፡፡

ይሁንና በደቡብ ሜጫ ወረዳ ገርጨጭ መንደር የማኀበረሰብ ተወካዮች በቀያቸው የሴቶችና ህጻናትን የወደፊት እድልና ተስፋ ያጨለመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማጥፋት የጀመሩት መልካም ተግባር በፅንፈኛ ሃይሎች  ሰይፍ ከመቀላት ግን አላስጣላቸውም፡፡

ፅንፈኛው ሃይል ለሰላም ካውንስሉ የተመለመላችሁ ናችሁ በሚል ፍፁም አረመኒያዊ በሆነ ሁኔታ ከተሳለቁባቸው እና ካሰቃዩዋቸው በኋላ የአራቱን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጥፈዋል፡፡

በፅንፈኛው ሃይል በግፍ የተገደሉት የገርጨጭ የማኀበረሰብ ተወካዮች የሰላም ካውንስሉ አባላት እንደልነበሩ የገለፁት አቶ አሰፋ ‘’ቢሆኑም ጉዳት የለውም ነበር’’ ምክንያቱም ካውንስሉ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ፣ ለማደራደር እና ለማወያየት ነው የተመረጠው፤ የትኛውንም አካል ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም አልነበረም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ 

በሰሜን ጎጃም ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ማህበረሰቡን በማወያየት የሰላም ካውንስል አባላት መመረጣቸውን እና ወደ ተግባር መግባታቸውን የገለፁት አቶ አሰፋ ገርጨጭ የሚባለው አካባቢ እሰካሁን የሰላም ካውንስል ለመምረጥ የማህበረሰብ ውይይት ያልተደረገበት ስፍራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top