ውሎች የተዋዋይ ወገኖችን ትክክለኛ ሀሳብ እና ፍላጎት የያዙ እውነተኛ መብት እና ግዴታ የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው። አንዳንዴ ግን እውነተኛ ውሎችን ለመሸፈን፣ ከሌሎች ግዴታዎች ለማምለጥ እና የሌሎች ውሎችን መፈፀም ለማሰናከል ተብለው የሚደረጉ ውሎች አይጠፉም። እስከ ፌዱራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ከማስመሰያ እና ከተንኮል ውል ጋር በተያያዘ ውሳኔ ያገኘ ክርክርን ቀጥሎ እንመለከታለን።
የቤት ሰርቶ ማስረከብ ውል
ወ/ሮ ኤልሳቤት ኤስ ኤን ኃ/የተ/የግ/ማ ጋር ጂ +1 ቤት ሠርቶ ስመ ሀብቱን ወደ ስማቸው አዙሮ በዘጠኝ ወር ውስጥ እንዲያስረክባቸው ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም ውል ይገቡና የቤቱን ዋጋ 4 ሚሊዮን 478 ሺ ብር ለመክፈል ይስማማሉ።
ሆኖም ኤስ ኤን ወ/ሮ ኤልሳቤት 3 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ከፍለውት የሚቀረው የተወሰነ ክፍያ ቢሆንም በውላቸው መሰረት ቤቱን አጠናቆ ስላላስረከባቸው፣ ቤቱን አጠናቆ ካርታውን በስማቸው አድርጎ እንዲያስረክባቸው እና ሳያስረክብ ለዘገየበት ጊዜም በወር አምስት ሺህ ብር ታስቦ እንዲከፈላቸው ክስ ያቀርባሉ።
ተከሳሹም ግንባታውን ማካሄድ ያልቻለው መንግሥት ግንባታ እንዳይካሄድ እስከ 2006 ዓ.ም በመከልከሉ ነው። ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ የሚቀርባቸውን ክፍያ ፈፅመው ቤቱን እንዲረከቡ ባስጠነቅቅም ገንዘብ የለኝም ብለው ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በውላችን መሰረት የከፈሉት ገንዘብ 3 ከመቶ ተቀናሽ ተደርጎ ከሚመለስላቸው በስተቀር ቤት ለማስረከብ ልገደድ አይገባም ሲል መልስ ሰጠ።
የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽ ክፍያውን ከፍለው የማጠናቀቅ ግዴታቸውን ስላልተወጡ ተከሳሽ ቤቱን ሊያስረክብ አይገባም ብሎ ቢወስንም፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀሪ ክፍያውን ከፍለው ተከሳሽ ለከሳሽ ቤቱን ሊያስረክብ ይገባል በሚል የሰጠው ውሳኔ እስከ ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ፀና።
የመቃወም አመልካቿ
አንድ በሌለሁበት የተሰጠ ውሳኔ መብቴን ጎድቷል የሚል ባለጉዳይ ውሳኔውን መቃወም የሚችልበት የሕግ አግባብ አለ። የመቃወም አመልካች ሆኖ ውሳኔውን በመቃወም። ከላይ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ እንዲረከቡት የተፈረደላቸውን ቤት ሊረከቡት አይገባም፤ ቤቱ ለኔ ተሽጧል ብለው ወ/ሮ ፍሬህይወት ውሳኔውን ተቃወሙት። ለወ/ሮ ኤልሳቤት እንዲያስረክብ በዚህ መዝገብ የተፈረደበትን ቤት ከዕዳ እና ከዕገዳ ነፃ መሆኑ ተረጋግጦ ኤስ ኤን መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም በውልና ማስረጃ በተመዘገበ ውል በ4.5 ሚሊዮን ብር ሸጦልኛል። ቤቱን ተረክቤም ግምባታውን በምፈልገው መጠን ለማጠናቀቅ ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጌበታለሁ ስለዚህ ከሳሽ እና ተከሳሽ ከሚኖራቸው የቤት ግንባታ ውል ግንኙነት በስተቀር ቤቱን ከተከሳሽ ላይ ገዝቼ ስለተረከብኩት ተከሳሽ ቤቱን ለከሳሽ እንዲያስረክብ በሚል የተሰጠው ውሳኔ ይሻርልኝ ሲሉ አመለከቱ።
ፍርድ ቤቱ ከግራ ቀኙ ክርክር ጉዳዩን ሲያጣራ ቤቱን ገዛሁት የሚሉት ወ/ሮ ፍሬህይወት ቤቱን ለወ/ሮ ኤልሳ አጠናቅቆ እንዲያስረክብ የተፈረደበት ኤስ ኤን ኃ/የተ የግ/ማ ግማሽ ባለድርሻ በመሆናቸው ለወ/ሮ ኤልሳ ቤቱን ላለማስረከብ ሆን ተብሎ የተደረገ የይምሰል ውል በመሆኑ መቃወሚያው ተቀባይነት የለውም ብሎ ውድቅ አደረገው።
በዚህ ክርክር ዙሪያ በተለያየ ደረጃ ሲካሄድ የነበረው ክርክርም ለፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቶበታል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱም በወ/ሮ ፍሬህይወት እና በኤስ ኤን ኃ/የተ/የግ/ማ መሀከል የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል የወ/ሮ ኤልሳቤትን መብት ለማሳጣት የተደረገ የይምሰል ወይም የተንኮል ውል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ይዞ ውሳኔ ሰጥቷል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ የብላክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላትን ትርጓሜ መሰረት በማድረግ የይምሰል ውል ማለት በተዋዋዮች መሀከል ምንም ዓይነት እውነተኛ መብት እና ግዴታ ሊፈጥር የማይችል ወይም ከእውነተኛው መብት እና ግዴታቸው ሌላ ለማስመሰያ የሚደረግ እና የሦስተኛ ወገኖችን መብት ሊጎዳ የሚችል ነው። ይህ ውል የውሸት ከመሆኑም በላይ እውነተኛውን ውል ለመሸሸግ የሚደረግ የማስመሰያ ውል ነው ሲል ትርጉሙን አስቀምጧል።
የተንኮል ውል ደግሞ አንድ ባለዕዳ ባለ ገንዘቡ በንብረቱ ላይ መብቱን እንዳያስፈፅም ጥቅም ለማግኘት ወይም ጥቅም ባያገኝም የባለገንዘቡን ሙብት ለማሳጣት በተንኮል ንብረቱን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚሸጥበት ወይም የሚያስተላልፍበት ውል ነው ሲል ያብራራዋል።
የተነሳው የቤት ክርክር በየትኛው የውል አይነት ውስጥ ሚወድቅ ይመስላችኋል?
የፌ/ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅፅ 25 ላይ ታትሞ በወጣው የሰ/መ/ቁ 207446 ላይ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ለወ/ሮ ኤልሳቤት በገባው ውል መሰረት ቤት ሠርቶ የማስረከብ ግዴታ ያለበት የኤስ ኤን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ከፊል ባለድርሻ ባለቤት ወ/ሮ ፍሬህይወት ቤቱ ክርክር እንዳለበት እያወቁ ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ ከተሸጠበት ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ መግዛታቸው ቤቱን የገዙት በመደበኛ እና እውነተኛ የግዢ ሀሳብ ሳይሆን ወ/ሮ ኤልሳ ቤቱን እንዳይረከቡ ለማድረግ ባለቤታቸው እና የባለቤታቸው ወንድም ድርጅት ከሆነው ከኤስ ኤን ጋር ያደረጉት የተንኮል ውል በመሆኑ ቤቱን ለወ/ሮ ኤልሳ እንዲያስረክብ የተሰጠው ውሳኔ ሊሻር አይገባም ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።