የኮሪደር ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገለፀ

6 Mons Ago 859
የኮሪደር ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገለፀ

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመዲናዋ ጽዳት እና ውበት የሚገነቡ መጸዳጃ ቤቶችን በመሥራት እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የኮሪደር ልማቱን እያገዘ መሆኑን ገለጸ፡፡

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኮሪደር ልማት ገጽታ አካል የሆነው የከተሞች መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ በጥራት እና በውበት በኢንዱስትሪ ፓርኩ እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡  

በወር ኪራይ ብዙ ገንዘብ ሊያስገኙ የሚችሉ የፋብሪካ ሼዶች በነጻ ለዚሁ ሥራ አውለናል ያሉት ኃላፊው፣ 3 ሺህ 800 ስኩየር ሜትር የፋብሪካ ሼድ ሊሆን የሚችል መሰረተ ልማት ለዚሁ ተግባር ማዋላቸውንና ይህም ለተለያዩ ድርጅቶቸ ቢከራይ በወር እስከ 10 ሺህ ዶላር ሊያስገኝ እንደሚችል አንስተዋል፡፡

ከ20 የሚበልጡ ኮንቴነሮችን ለፕሮጀክቱ ሥራ ውለዋል የሚሉት አቶ ትንሳኤ፣ ተጨማሪ 10 ኮንቴነሮች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለከተማዋ እድገት እና ለውጥ እየተገነቡ ላሉት መሰረተ ልማቶች እንደ መብራት እና ውሃ ያሉ ድጋፎች እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡

አክለውም፣ "የተለያዩ የድጋፍ መዋጮችን ከማድረግ ጀምሮ ለከተማዋ ውበት እና ጽዱ መሆን ተቋማችን እየሠራ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ ለመጸዳጃ ቤት የሚሆኑ ኮንቲነሮችን፣ ማምረቻ ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ውሃ እና መብራት እያቀረበ መሆኑ 24 ሰዓት የሚሠራውን የኮሪደር ልማት ሥራ እንዳቀላጠፈውም አመላክተዋል፡፡ 

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለኮሪደር ልማቱ የኮንስትራክሽን አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት ድጋፍ እንደሚያደረግላቸው ኃላፊው አንስተው፣ ሌሎች ተቋማትም በተመሳሳይ መልኩ በልማት ሥራዎቹ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

ግንባታዎቹ ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸው እና የተለፋባቸው በመሆናቸው ኅብረተሰቡ በእኔነት ስሜት ሊጠቀምበት፣ ሊከታተል እና ሊጠብቅ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top